የማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች መግለጫ እና ለትናንት ያላቸው ፍቅር !
ሲሳይ አጌና
የማህበረ ቅዱሳን አመራሮች በማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን በቅርቡ ስላወጡት መግለጫ የሰጡትን ማብራርያ የተከታተልኩት ዘግይቼ ነው።ስለ መግለጫው የቀድሞ አመራሮች (ከአንዱ በቀር) ማብራርያ የሰጡበት እና ሌሎቹ ያልተገኙበት ምክንያት ግን አልተገለፀልንም።(ክፍል 1 እና ክፍል 2 ይመልከቱ) የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ እና የቀድሞ አመራሮች ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ እና ዲያቆን ብርሃኑ አድማሴ መግለጫ የሰጡት በቅርቡ ያወጡትን አነጋጋሪ መግለጫ በተመለከተ እንደሆነም ግልጽ አድርገዋል።
የማህበሩ አመራሮች ከሰብሳቢው ውጭ ያሉት ያልተገኙበት እና የቀድሞዎቹ ምላሽ የሰጡበት ምክንያት መግለጫውን የአሁኑ አመራር ብቻ ሳይሆን እኛም እናምንበታለን የሚል የአጋርነት መግለጫ ወይንም ተባባሪነት ሊሆን ይችላል።ወይንም መልዕክቱን ይበልጥ መስደድ የተፈለገበት አካባቢን ታሳቢ አድርጎም ሊሆን ይችላል።ምንም ይሁን ምን ለጉዳዩ ማብራርያ መስጠታቸው ይበልጥ ነገሮችን ግልፅ አድርጓል።
መልዕክታቸውን ሳትረዱ ለትችት ቸኮላችሁ የሚል አስተያየት ለሰጡ ወገኖች የማህበሩ አመራሮች ከተፃፈው በላይ ከባድ መልዕክት እና ጠንካራ ተቃውሞ እንዳላቸው አሳይተዋቸዋል።ይህንን መልዕክት ሰምቼ በዝምታ ማለፍ በፍፁም ስላልቻልኩ የሚከተለውን አስተያየትና ጥያቄ አቀርባለሁ።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መከራ የቀጠለ ቢሆንም፣በማህበረ ቅዱሳን መግለጫ እነደተመለከተው ግን በምንም መመዘኛ ቤተክርስቲያኒቱ ከትናንቱ የከፋ አደጋ አልተደቀነባትም። ሆኖም ምናልባት አደባባይ ያልወጡ እነሱ እና የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ብቻ የሚያውቋቸው አደጋዎች ይኖሩ ይሆን? ምናልባት ከዚህ ቀደም በሕወሃት ዘመን እንደነበረው በአቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት እንደሚያደርገው ሁሉ ዛሬም ቤተክርስቲያኒቱ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ ወይንም በሌላ የደህነነት ባላስልጣን ቁጥጥር ሥር ነችን?ሌሎች ያላየናቸው እና ያልሰማናቸው ቤተክርስቲያኒቱ የተጋፈጠችው ፈተና ፣ምዕመናን የተደቀነባቸው አደጋ አለን? እንደሰማኋቸው ግን ከምናውቀውና ከሰማነው በላይ የነገሩን ምንም የተለየ አደጋ የለም።ይልቁንም መግለጫውን ባጮሁት ልክ የሚዘረዝሩት አደጋ ማቅረብ ሲቸግራቸው ቤተክርስቲያኒቱን የማዳከም ሴራ አለ የሚል ፍንጭ እንኳን ያልቀረበበት ተጨባጭነት የሌለው መላምት ሰንዝረዋል።የአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ማህበር መሪዎች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚራገብ እና ማሰብ ለሚችል ሰው የማይመጥን ሸቀጥ ይዘው አደባባይ መውጣታቸው እነርሱ ፈቅድው የገቡበት ቢሆንም ማህበሩን ግን በፍፁም አይመጥንም።"አዲሲቱ ኢትዮጵያ የሚባለው ቤተክርስቲያኒቱን ለማደካም" ነው የሚል መጠየቅ ለሚችሉ እና ከህሊናቸው ጋር ለሚኖሩ የሚያስገምት ትንተና መስጠትም ከበስተጀርባው ምን ይዟል የሚል ጥያቄም ያስነሳል።
በዘር ፖለቲካ ስትታመስ፥በአምባገነን አገዛዝ ስትቀጠቀጥ የኖረች እና የዕምነት ተቋማት የተዋረዱባት ሃገር ከዚህ አዙሪት እንድትወጣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሎ መመኘትና ለዚያ መስራት ያስከብራል እንጂ ያስወቅሳልን ? ባይሆን በተግባር እንዲፈፀም ማበረታታትና ሥርዓቱ ወደ ትናንት እንዳይመለስ መታገል ያስፈልጋል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስንም ሆነ ሌሎች የዕምነት ተቋማትን ማጠናከር ወደ አውሬነት የተለወጡ ወጣቶችን በመመለስ፤ ሞራልና ሥነምግባር ያለው ፥ሃገር የሚረከብ ትውልድ እንዲያብብ የሚያደርግ በመሆኑ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስንም ሆነ ሌሎችን ዕምነት ላጥፋ ብሎ በራሱ ላይ ጥፋት የሚያውጅ ኢትዮጵያዊ መንግስት ይኖራል ተብሎ አይታመንም። የኢትዮጵያ መንግስት እና ኢትዮጵያዊ መንግስት ልዩነቱ ግልፅ ይመስለኛል።ጫፍ የሌለው የፌስ ቡክ ወሬ በተከበረ ማህበር ስም ማስተጋባት ማህበሩን አይመጥንም።
ግን ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያ ሁሉ መዓት ሲወርድባት የትነበራችሁ? ብዬ አልጠይቅም።መፍራት ወይንም ቤተክርስቲያኒቱ እየተጎዳችም ቢሆን ቅዝምዝሙን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ እንደ ግለሰቦች ጥንካሬ እና መንፈሳዊነት መጠን ስለሚወሰን መፍራት ቢያስወቅስ እንኳን ወንጀል አይደለም እና እንለፈው።ያልገባኝ ግን የዛሬውን የቤተክርስቲያኒቱ ችግር እንዲህ የሚያንገበግባቸው ወገኖች፣ የትናንቱን የሚታየውን እና የሚዳሰሰውን የሕወሐት ዘመን ጨለማ በአፈ ታሪክ የሰማነው ይመስል ሊክዱት ወይንም ሊያደበዝዙት የፈለጉበት ምክንያት በፍፁም ሊገባኝ አይችልም።ምናልባት በቅንነት ካየነው በዚያ ድቅድቅ ጨለማ የት ነበራችሁ? የሚለውን ጥያቄ ለመሸሽ ሊሆን ይችላል።ነገሩ ግን በቅንነት አይመስልም። ሁለት የተከፈለችው ቤተክርስቲያን አንድ የሆነቸው፣የተሰደዱትም ፓትርያርክ ብጹዕ አብነ መርቆርዮስ የተመለሱት በለውጡ ስለመሆኑ ለተነሳው አስተያየት የሰጡትን መልስ ስሰማ ጉድዩ ከቤተክርስቲያን ባሻገር ነውን ? የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል።”ፓትርያርኩን ያባረረውም ፣ የመለሰውም ራሱ ኢህአዴግ ነው” የሚል ዕውነት ላይ የጨፈነ ምላሽ መንፈሳዊ ማህበር ከሚመሩ ሰዎች አይጠበቅም.።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከለውጡ ወዲህ ያለውን መንግስት ኢሕአዴግ (ለ) ፣ ሟቹን ኢሕአዴግ (ሀ) እያሉ የሚጠሩት ዕውነቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን ፣ በገዢው ፓርቲ ላይ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር መሆኑ ግልፅ ይመስለኛል።አንዳንዶች ይህቺን በግንዛቤ ዕጦት ሲያነበንቧት ፣የግንዛቤ ችግር የሌለባቸው እና ፖለቲካኛ የሆኑ ግን ለፖለቲካ ፍላጎታቸው ሲሉ ሲያስተጋቡት አድምጠናል።የግንዛቤ ችግር ሳይኖርባቸው እንዲሁም ፖለቲኛም ሳይሆኑ የሕወሃትን አገዛዝ ከብልፅግና ጋር አንድ አድርገው የሚመለከቱ የማህበረ ቅዱሳን አመራሮችን የመሳሰሉ ግን ምን እንደሚባሉ አላውቅም።
ማንም ማመዛዘን የሚችል ሰው እንደሚረዳው ትናንት የነበረው የሕወሓት አገዛዝ ሲሆን፥ ዛሬ ደግሞ ያለው ሕወሃትን ከስልጣን አባሮ ፣ፓርቲውን አሸባሪ ብሎ የፈረጀ የብልፅግና ፓርቲ ነው።ሩብ ክፍለ ዘመን የተከፈለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነቷን ያገኘችው እና ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ በክብር ሃገራቸውን የረገጡት እና ወደ መንበራቸው የተመለሱት ሕወሃት ከቤተመንግስት በመውጣቱ መሆኑ ለሚያይ ሁሉ በብርሃን ላይ የተሰጣ ዕውነት ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን የደረሰባትን መከራ እና ሰቆቃ ፣የጅምላ ፍጅት እና ካሕናት አይናቸው ታስሮ ወደ ገደል የተጣሉበትን አሰቃቂ ትዕይንት ከዛሬው ይሻላል ብለው የማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች ሲከራከሩ ሳይ ማመን ነው ያቃተኝ። ያኔ ስላልነበሩ ወይንም ስለሚፈሩ ባይከታተሉት እንኳን ፥ ትናንት ቤተክርስቲያኒቱ ያሳለፈችውንና የተመዘገበውን ሰቆቃ እንደምን ማገላበጥ አቃታቸው? ትናንት በቤተክርስቲያኒቱ እና ምዕመናኑ ላይ የሚፈፀመው ሰቆቃ የሚመዘገበው በግል ጋዜጦች ፣በሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ኢሰመጉ እና በፖለቲካ ድርጅት ልሳናት ስለነበር በወቅቱ ላይመለከቱት ይችላሉ።ይህንን እንድል ያስደፈረኝ የማሕበረ ቅዱሳን አመራር የነበሩ ሰው ከለውጡ በፊት ግዮን መፅሄት ላይ ባሰፈሩት እና በኋላም በኢንተርኔት በተሰራጨው ፅሁፋቸው እንደገለፁት የማህበረ ቅዱሳን አመራሮች የግል ጋዜጦችን ማህበሩ እንዳይገዛ ይከላከሉ ነበር።ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት መንግስት ማህበሩን ለማፍረስ ሰበብ ያገኛል የሚል ነው። ከዚህ ስንነሳ ምናልባት የትናንቱ ድቅድቅ ጨለማ ያልታያቸው ማህበሩ እንዳይፈርስ የሚፈፀመውን ላለማየት እና ላለመስማት በመወሰናቸው አሊያም ምናልባትም ብዙሃኑ በጥቂቶች ፍላጎት ውስጥ በመውደቃቸው ሊሆን ይችላል።ሆኖም ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀውን ውይይት ሳደምጥ ከመረጃ ክፍተቱ ይልቅ ሥልጣን ላይ ባለው መንግስት ላይ ያላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የትናንቱን እንዳያያቱ የጋረዳቸው ይመስለኛል።ምናልባትም የሕወሓት ሥርዓት በመወገዱ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የሃገሪቱን ከተሞች በደስታ ሰልፍ ሲያጥለቀልቅ ፣እነርሱ ካልተደሰቱት ወይንም ካዘኑና ከተቆጩት ውስጥም ሊሆኑ ይችላሉ፥ዘመንፈስን ጨምሮ ማለቴ ነው።
ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ችግር የሕወሃትን የጭለማ ዘመን ከመጥቀስ ይልቅ ወደ ኋላ 50 ዓመት መሄዳቸው ይበልጥ የገባኝ ቃለምልልሱን ከተከታተልኩ በኋላ ነው። ከንጉስ ኃ/ሥላሴ መንግስት ፍፃሜ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱ ሚና መቀነሱና ዕኩልነት መታወጁ ግልፅ ነው።የደርግ መንግስት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን አስሮ መግደሉም ይታወቃል።ነገር ግን የወንጌላውያን ቤተክርሲያን መሪ የሆኑትን ቄስ ጉዲና ቱምሳንም በተመሳሳይ አስሮ ገድሏል።ምዕመናን በዕምነታቸው ተለይተው የሚታረዱበት፣አብያተ ክርስቲያናት የሚነዱበት ሁኔታ ግን አልነበረም።
የሕወሃት አገዛዝ ሲመጣ ደግሞ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን ከመንበራቸው አባሮ፣በአቡነ ጳውሎስ የተካበት፥አርሲ አርባ ጉጉ የጀመረ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ውድመት፣የምዕመናን ዕልቂት 27ቱንም ዓመት በዙር አሰቃቂ በሆነ መንገድ የቀጠለበት እና አያሌ ሺዎች የረገፉበት ነበር ።በማናቸውም መመዘኛ ቢታይ በቅርብ ታሪካችን እንደ ሕወሃት ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብርቱ ፈተና አልገጠማትም።
የአሰቦት ገዳም 16 መነኩሴዎች አይናቸው ታስሮ ጥይት እየተተኮሰባቸው ወደ ገደል እየተነዱ ያለቁት በሕወሃት ዘመን ነው።የፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን ከሥልጣን መነሳትን ተቃውማችኋል በሚል ጳጉሜ 1/1985 በቁጥር 18 የሚሆኑ የጎንደር ኢየሱስ ካህናት እና ምዕመናን በቤተክርስቲያናቸው ቅጥር ግቢ የተጨፈጨፉትም በሕወሃት ዘመን ነው።ጥር 17 /1989 ዓ/ም ባህታዊ ፈቃደ ሥላሴ በአዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን ታቦተ ሕጉ በቆመበት በጥይት የተገደሉት በሕወሃት ዘመን ነው።የቤተክርስቲያናችንን ሙዳየ ምፅዋት አናዘርፍም ያሉ የልደታ ቤተክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን በአዲስ አበባ ከተማ የፌደራል ፖሊስ ጥይት የዘነበባቸው እና ቢያንስ አንድ ስንታየሁ የተባለ ወጣት የተገደለውና ሌሎች ወደ ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ የተጫኑትም በሕወሓት ዘመን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ከ5 ኪሎ እስከ ላፍቶ መኖሪያ ቤታቸው በሕወሐት ደህንነቶች በራቸው እየተደበደበ ጥቃት የተፈፀመባቸው በሕወሃት ዘመን በሃምሌ ወር 2001 ዓ.ም ነበር። በነሃሴ ወር 2004 ዓ/ም አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ለቤተክርስቲያኒቱ ችግር እግዚአብሄር መልስ ሰጠ ብለው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሃገር እንዲገቡ የፃፉትን ደብዳቤ እንዲስቡና የቤተክርስቲያንቱ አባቶች ሁለት ቦታ ተከፍለው እንዲቀሩ እና አዲስ ፓትያርክ አዲስ አባባ እንዲመረጥ የተወሰነው በሕወሃት መሪዎች ነው።
አስደንጋጭ በሆነ መንገድ የምዕምናን ቁጥር እየቀሰ የሄድውም በሕወሓት ዘመን ነው።የደርግ መንግስት በ1976 ባካሄደው ሕዝብ እና ቤት ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 38 ሚሊዮን 203 ሺህ 681 የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጠው ወይንም 54.2 በመቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሲያን አማኞች ነበሩ።ሕወሃት ሥልጣን በያዘ 3ኛው ዓመት በ1987 በተካሄደ ቆጠራ የኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ቁጥር ወደ 4 በመቶ ወርዶ 50.6 በመቶ ዝቅ አለ።ከ10 ዓመት በኋላ
በ1999 በተካሄደ ሕዝብና ቤት ቆጠራ እንደገና 7.3 በመቶ ቀንሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች ቁጥር ወደ 43 .5 በመቶ ወረደ።ለማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች የተሻለ የነበረው የሕወሓት ዘመን ለኦርቶዶክሳውያኑ ግን ጭለማ እንደነበር ከብዙ በጥቂቱ የተዘረዘሩት በግልጽ ይነግሩናል።
ሕወሃት ተሽንፎ ቤተመንግስቱን ለቆ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሲያፈገፍግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነት ታወጀ።ሩብ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ውሳኔ ተገፍተው የተሰደዱት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ እና ጳጳሳት ወደ ሃገር ቤት በክብር ገቡ።ዋሺንግተን ዲሲ በተካሄደው የዕርቅ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን ወደ ዋሺንግተን በበረሩበት አውሮፕላን ይዘው ተመለሱ።ኦርቶዶክስ ሃገር ናት ሲሉም የቤተክርስቲያኒቱን ግዝፈት እና ሚና መሰከሩ።
እርግጥ ከለውጡም በኋላ ዚጎች በዕምነታቸውና በብሄራቸው ተለይተው ተገድለዋል።በአሰቃቂ ሁኒታም ታርደዋል። በዘረፋ እና በማውደም የማደሕየት ርምጃዎች መወሰዳቸውም ግልፅ ነው።የድርጊቱ ፈፃሚዎችም በዕምነት እና በብሄር አክራሪነት የተለከፉ የሥርዓቱ ተቃዋሚዎች መሆናቸውም የዚያኑ ያህል ግልፅ ነው።የግፍ ድርጊቱ ተባባሪዎች ምናልባትም አስፈፃሚዎች ጭምር በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተገልፆ ከንቲባዎች፡ አስተዳዳሪዎች እና ሌሎች ባለስልጣናት ከሥልጣን ተሽረው ወህኒ መወርወራቸውም ይፋ ሆኗል። ከሃጫሉ ግድያ በኋላ ድርጊቱ ብዙም ሲቀጥል የማናየው፣ሃጫሉ በተገደለበትም ወቅት ጥቃቱ በተወሰነ አካባቢ ብቻ መጠንከሩ የመንግስት መዋቅር እየፀዳ በመገኘቱና አክራሪዎቹ በመመንጠራቸውም እንደሆነም ይታመናል።
የማህበረ ቅዱሳን መሪዎች ትናንት ያ ሁሉ መዓት ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ሲወርድ ምንም ያላላችሁት ፥ መቃወም ዋጋ ስለሚያስከፍል ሊሆን ይችላል።ለዕምነት ሲባል የሚመጣውን ሁሉ መቀበል የሚገባ ቢሆንም ፣አንዳንዴ ቅዝምዝሙን አጎንብሶ ማሳለፍ እንደ ጥበብ የሚመለከቱት መኖራቸው እርግጥ ነው። ያን ሁሉ ጨለማ የታገሰ ቡድን የዛሬው ነፃነት ይበልጥ ምክንያታዊ እንዲሆን ሊያደርገው በተገባ ነበር። ምክንያታዊነት ማለት ጥቃቱን ማን ለምን ዓላም ይፈፅመዋል የሚለውን መጠየቅ እና እንዴት ይቁም የሚለውን መመርመር ጭምር ነው።
የማህበረ ቅዱሳን አባላትን “በንቃት ተከታተሉን” የሚል ጥሪ ማስተላለፍ ለተሸነፉ እና ለሸሹ እንዲሁም ለሃገራችን መዓት ለሚመኙ ያስደስት ፣ያስጨበጭብ ይሆናል ። ከሌላው አማኝ ጋር ተዋህዶ በዳር ሃገር ለሚኖረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኝ ግን የሞት ድግስ ጥሪ መሆኑን ክቃለምልልሱ ይበልጥ መረዳት ይቻላል።አሻግሮ ማየት ለሚችል በሃገር ላይ ቀውስ በበረታበት ግዜ እንደ ሕወሃት ያለ በግልፅ የቤተክርስቲያኒቱ ጠላት የሆነ መንግስት ቢሆን እንኳን ሕግና ሥርዓት እንዳይፍርስ መንግስት መኖሩ የግድ ይላል።ሕግና ሥርዓት ሲፈርስ ዕልቂት ይነግሳልና!
ግንቦት 11/2013 (May 19/2021)