በኢትዮጵያ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ለውጥ በብዙ ፍላጎቶች እንዲሁም ሥልጣናቸውን በተነጠቁ ወገኖች እና የፖለቲካ ንግድ ላይ በቆዩ ሃይሎች ፈተና እየገጠመው መሆኑ ግልጽ ነው።ይህ ዛሬ የሚታየው መንገጫገጭ ግን የትናንቱን የመቃብር ሕይወትና የመቃብሩን ጥልቀት በፍጹም ሊያስረሳን አይገባም።
ኢትዮጵያውያን ያለፍንበትን መከራ በማሰላሰል ብቻ ሳይሆን መውጫችን ምንድነው ብለን የተጨነቅንበትን ግዜ መልሰን ስንቃኝ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ በጉንፋን የሚመሰል ቀላል ሕመም ሲሆን፥በየአካባቢው ያለው ቆሻሻ ድርጊት ከቀጠለ እና የዕልህ ጉዞው " በእኛ እና እነሱ" ቅኝት ከዘለቀ ግን ጉንፋኑ ተስቦ ሆኖ ሁላችንንም እንደሚያጠፋ ከጥርጣሬ ባሻገር መናገር ይቻላል።መንግስት የየአካባቢው ጉልበተኞችን እንዲያስታግስ ፥ ሕዝቡም ራሱን ከጎበዝ አለቆች ስብከት እንዲጠብቅ መወተወቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።ጨለማ መልሶ እንዳይወርሰን ከጨላማ ሰባኪዎች ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል። ትናንት የነበርንበትን ጨለማ ብቻ ሳይሆን፥ ከጨለማ ለመውጣት የነበረው መንገድ ሁሉ በራሱ ጽልመት የወረሰው መሆኑን በማስታወስ ዛሬን በከፍተኛ ሃላፊነት እና ጥንቃቄ እንድንጓዝ ግድ ይለናል።
በዛሬው (መጋቢት 30/2011) "ለውጥማ አለ!?" በሚል ርዕስ በዚህ በብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ "ብራና" ባዘጋጀው መድረክ አርዕስቱን መሰረት አድርገው የሚነሱ ጥያቄዎችን በተለይም ለውጥ የለም በሚል የሚሰሙ ድምጾችን በቀጣዮች ነጥቦች እናስልለውና (እናድክመውና) የለውጡን ትርጉም ከለውጡ ዋዜማ ሁኔታ አንጻር እንፈትሸው።
አሸባሪ የተባለው ሚዲያ "ኢሳት" ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ ብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ ከናንተ ጋር እየታደመ ፥የሃገሪቱ ወህኒ ቤቶች ከፖለቲካ እስረኞች በጸዱበት፥ ጠመንጃ ያነሱትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሃገራቸው በተመለሱበት ፣ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ለሁለት የተከፈለቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነቷ በተረጋገጠበትና መንበራቸውን በፖለቲከኞች ውሳኔ የተነጠቁት ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ ሥፍራቸው በተመለሱበት፥የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ወህኒ የተቆለፈባቸው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ስለዕምነታቸው በነጻነት በመስጊዳቸው በሚወያዩበት ፣ እንደ ርሥት 27 ዓመታት በሙሉ በአንድ ሰፈር ሰዎች በባሌበትነት የተያዙ የሥልጣን ቦታዎችን ሌሎችም ሲከፋፈል እያየን፣ አሳሪዎች በወንጀል ተጠርጥረው እነርሱም በተራቸው ውህኒ ገብተው አቤቱታ ሲቀርቡ እየሰማን ወዘተ ለውጥ የታለ ብሎ የሚጠይቀውን ፥በግሌ ለውጥ ምንድን ነው ማለቱን መርጬያለሁ።
ይህ ለውጥ ካልሆነ ምን ብለን እንጥራው ይሆን ስያሜ ይስጡን እና እንሟገትበት።
በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ትርጉም የሚኖረው መቃብር ውስጥ ለነበረው ሁሉ ቢሆንም ፥የመቃብሩን ጥልቀት ይበልጥ የሚረዳው ግን ከመቃብሩ ውስጥ ለመውጣት የተፍጨረጨረውና መውጫውን ያሰላሰለው ብቻ ነው።
ይህንን ከላይ እንደጠቀስኩት የራሴን አጋጣሚ በማንሳት ላብራራው።
በምኖርበት አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት "ሊዝበርግ ፓይክ "በተባለ መንገድ ላይ የሚገኝ "ስታር ባክስ" የሚሉት ቡና መሸጫ አለ።ይሄ ቤት በብዛት የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ዜጎች ይሰባሰቡበታል።ምናልባትም ሞቃዲሾ ያላችሁ ያህል እንዳይሰማችሁ የሚያደርገው ሞቃዲሾን አለማውቃችሁ ወይንም ጥቂት ነጮች እንዲሁም ስፓኒሾች እና የኤዢያ ሰዎች በማየታችሁ ሊሆን ይችላል።
ታዲያ እዚህ ቡና መጠጫ ሱቅ ውስጥ ሁልግዜ ሶማሊያውያን ተሰብስበው ሳይ ሃገር አልባነታቸው ይመጣብኛል። በሕይወቴ ተስፈኛ የሆንኩትን ሰው ተስፋ ቢስ ያደርጉኝ እና ኢትዮጵያን መልሼ ማግኘቴ ወይንም ማየቴ ከነአካቴውም ኢትዮጵያ በሕልወናዋ መቀጠሏ ያጠራጥረኛል።እናም ከዚህ ቡና መሸጫ ትኩሱን ቡና ይዤ ስወጣ በበጋ ሙቀት ብርድ ብርድ እያለኝ ፥ፊቴ ጭጋግ ለብሶ መፍትሄው ምን ይሆን ?እያልኩ ይበልጥ አሰላስላለሁ።
ሥልጣን ላይ የነበረው ቡድን እና መንግስት እንደሚወድቁ ጨርሶ ተጠራጥሬ ባላውቅም የሚተካቸው ማነው? ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ጥላቻ በተሰበከበት እና ተረት ታሪክን በተጫነበት ሃገር ፥ልዩነት ጌጥ እና ውበት መሆኑ ቀርቶ የጥላቻ እና የግጭት መንስኤ እንዲሆን መንግስታዊ እና የፓርቲ መዋቅር በሚተጋበት ሃገር አፋኙ እና ዘረኛው ሥርዓት ሲወገድ የሚተካው ማነው ? እንዴትስ ይወገዳል ? የሚለውን ብርቱ ጥያቄ እያሰላሰልኩ በዚሁ በቨርጂኒያ "ሊዝበርግ ፓይክ" ጎዳና ተመላልሺያለሁ።
ብዙ ሳስብ ፥የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ሥመረምር ከብርሃን ይልቅ ጭለማው እየበረታብኝ ፣ያለንበት የመቃብር ጥልቀትም ይበልጥ እየተገለጸልኝ መጣ ። ከሃገሬ የራቅኩት 12 ሺህ ያህል ኪሎሜትር ቢሆንም ውስጤ የገባው ሥጋት ኢትዮጵያን ጨርሶ የማልደርስባት አደረገኝ። ከማርስ በላይ በአያሌ ሚሊዮኖች ኪሎሜትር ኢትዮጵያ ራቀችብኝ። እንዴት ልድረስባት? ማን እንዴት ከዚህ መከራ ይገላግለን? መፍትሄ ፍለጋ አማተርኩኝ።አማራጭ ማሰስ ጅርመርኩኝ።
1ኛ/ከኤርትራ የሚነሱ አማጽያን ከዚህ መከራ ይገላግሉን ይሆን? በሚል እነርሱ ላይ በማተኮር አቅማቸውን፥ትብብራቸውን እና የኤርትራን መንግስት ድጋፍ ለመመርመር ሞከርኩኝ።እነዚህ ብረት ያነሱና የኤርትራን መንግስት ከለላ ያገኙ አማጽያ አርበኞች ግንቦት 7፣ኦነግ፣አዲሃን፣ትህዴን፥ ARDUF፣ONLF ወዘተ በጋራ ቢሰሩና የትብብር ግንባር ቢፈጥሩ ሥርዓቱን በሃይል አሰውግደው ሥልጣን መያዝ ይችላሉ ወይ ለሚለው ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ሥርዓቱን ለመጣል የሚያስችላቸው ቢሆንም ፥ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ እና መረጋጋት የሚወስድ መሆኑ ግን አጠራጣሪ ብቻ ሳይሆን አስፈሪም ነበር።
ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ በመዳከሙ እንዲሁም በሙሉ ልብ እና በግልጽ አማጽያኑን የሚረዳ የጎረቤት ሃገር መንግስት መኖሩ ብረት ያነሱት የኢትዮጵያ ሃይሎች በቀላሉ እና በፍጥነት የማሽነፍ ዕድል እንደሚኖራቸው በኡጋንዳ ሚልተን አቦቴ በኋላም ይዌሪ ሙሰቬኒ እንዲሁም በኮንጎ ሎራን ካቢላ በታንዛንያ እና በርዋንዳ መንግስታት ድጋፍ በወራት እንቅስቃሴ ኢንቴቤ እና ኪንሻሳን መቆጣጠራቸውን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል።
ችግሩ ብረት ያነሱት የኢትዮጵያ ሃይሎች የተበታተኑ እና ተባብረው ለመስራት አለመፈለጋቸው ነው፥በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ኢትዮጵያ ከሚሉ ሃይሎች ጋር ለመንቀሳቀስ አለመፍቀዱ በኢትዮጵያ በወታደራዊ ሃይል መንግስት በመቀየር የተረጋጋ ሃገር ለመፍጠር እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ያለውን ዕድል ብርቱ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶት ቆይቷል።ቡድኖቹ ተነጣጥለው ቢሄዱ እና ተሳክቶላቸው ቢያሸንፉ እንኳን ኦነግ ከኦሮሚያ ክልል ውጭ ተቀባይነት አይኖረውም።በሌላም በኩል አርበኞች ግንቦት 7 ቢያሸንፍ ሀገሪቱን በበከላት የዘር ፖለቲካ ሳቢያ ይህ ቡድን ቢያንስ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል ተቀባይነት ማግኘቱ በእጅጉ አጠራጣሪ ነው።እንደተበታተኑ በየሰፈራቸው ቢያሽንፉ ድግሞ ሃገሪቱ ባልተቁረጠ የዕርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መዘፈቋ የማይቀር ይሆናል።
ሥለሆነም በወታደራዊ ሃይል የነበረውን ሥርዓት ማፍረስ ቢቻልም፥የተርጋጋ ሃገር እና መንግስት ማምጣት እንደማይቻል ሲታየኝ ከመከራ የምንፈታበት፥ መዳኛችን ምን ይሆን በሚል ሌላ መውጫ አሰላስላለሁ።
2/ሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማስወገድ ያለው ሌላው አማራጭ ሕዝባዊ ዓመጽ ወይንም ሕዝባዊ ዕምቢተኝነት ነው።ሕዝባዊ ዓመጽ ደግሞ በመጨረሻው ምዕራፍ መልክ የሚይዘውና ፍጻሜ የሚያገኘው በወታደሩ ጣልቃገብነት እና ግፊት መሆኑም ይታወቃል።በኢትዮጵያ ያለው ወይንም የነበረው የሰራዊቱ አደረጃጀት እና አመራሩ ሲታይ በሕወሃት ፍላጎት የተዋቀረ እና በሕወሓት ታጋዮች ቁጥጥር ሥር የሚገኝ በመሆኑ የሕወሓትን አገዛዝ ለማስወገድ የሚደረግን ትግል እንኳን ደግፈው ሊቆሙ ገለልተኛ ሆነው እንኳን እንድማይታዘቡ ይልቁንም ወደ ጭፍጨፋ ሊያመሩ እንደሚችሉም ሳይታለም የተፈታ ነው፥በተግባርም ያየነው ይህንኑ ነው።
ከ15 ዓመታት በፊት በዩክሬን ኬቭ እና በጆርጂያ ቲቢሊሲ ጎዳናዎች የታየው ኦሬንጅ እና ሮዝ ሪቮሉሽን(የብርቱካን እና ጽጌረዳ አብዮት) እንዲሁም በቅርብ ዓመታት እ/ኤ/አ በታህሳስ 2010 በቱኒዚያ የተነሳው እና በአረቡ ዓለም በተቀጣጠለው የሞሃመድ ቡዓዚዝ አብዮት ዙፋናቸው ላይ ሲንገታገቱ የነበሩት አምባገነኖች ወንበራቸውን የተነጠቁት በወታደሩ ጣልቃገብነት አሊያም ዓመጹ ባስከተለው የትጥቅ ትግል መሆኑ ይታወቃል።
ሕዝባዊ ዓመጹ ወደ ትጥቅ ትግል ያመራባቸው ሊቢያ እና የመንን የመሳሰሉ ሃገራት ደግሞ አምባገነኖቹን ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊን እና አሊ አብደላህ ሳላን ቢገላገሉም ሃገራቱ አሁንም በቀውስ ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።ሕዝባዊ ዓመጹ ብቻውን መፍትሄ ያስገኘባቸውን ሃገራት ግብጽን እንድምሳሌ ብንወስድ እንኳን ሕዝባዊ ተቃውሞው የተገታው እና የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ስንብት የተከተለው በወታደሩ እና በጸጥታ ሃይሉ ጣልቃገብነት ነው።
ከላይ እንደተመለከትነው በኢትዮጵያ የነበረውን የወታደሩን አወቃቀር ስንመረምር በሕዝባዊ ዓመጽ ለለውጥ የሚነሳውን ሃይል ወታደሩ የሚደግፍ ሳይሆን ፥የሚጨፈልቅ በመሆኑ በሕዝባዊ ዓመጽ በኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣትን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ታዲያ እንዴት ለውጥ ሊመጣ ይችላል? ስል ቆይቺያለሁ።በወታደራዉ መፈንቅለ መንግስት ለውጥ እንዳይመጣ አመራሩ በሕወሓት ሰዎች በመያዙ ከላይ ግልበጣ ማድረግ የማይታሰበውን ያህል፥ከሥር የሚነሱ ዝቅተኛ መኮንኖችም በዘር በተከፋፈለ ሰራዊት ውስጥ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ዕድላቸው ዜሮ ነው ማለት ይቻላል።ቢሳካለቸው እንኳን ሰራዊቱ በዘር ተከፋፍሎ ይታኮሳል እንጂ ሕወሓትን ከቤተ መንግስት ማውጣት አይቻለውም።
ታዲያ ሃገሪቱ ወደ ቀውስ ከምታመራ ዘረኝነት እና ዘረፋን የአመራር ፍልስፍናቸው ያደርጉት ሕወሓቶች የጫኑብንን ባርነትን ፈቅደን፣ዘረፋውንም ይሁንላቸው ብለን ብንተዋቸውስ እንኳን ሃገሪቱን ብድር ማጥ ውስጥ ከተው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ፈተና ላይ የጣሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ በመውደቃችን ፥እነሱም በሥልጣን ኢትዮጵያም በሕልውናዋ መቀጠሏ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
እንዲህ ግራ ተጋብቼ ፥ዕይዝ እጭብጠው ቸግሮኝ ባለሁብት እና እንደጎረቤት ሶማሊያ ዜጎች ሃገር አልባነት እየተሰማኝ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ዓመጽ ተስፋ ቢዘራብኝም መድረሻው የት ይሆን የሚል ብርቱ ስጋትም አልተለትልየኝም ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዓመጽ ከግብጽ እና ቱኒዚያ የተለየ፣ ከሊቢያ እና የመን የባሰ አደጋ የሚደቅን በይበልጥም ወደ ሶርያ የተጠጋ መሆኑ ይታየኝ ነበር።በሶርያ በአንድ ዕምነት ተከታዮች ማለትም "የሺአ" ሙስሊሞች ውስጥ "አለዊት" የሚባለው ሴክት ወይንም ክፍል የሃገሪቱን መሪነት፣ ጸጥታ እና መከላከያ በመቆጣጠሩ ሕዝባዊውን ዓመጽ በጉልበት ለመጨፍለቅ ተንቀሳቀሰ ፥በውጤቱም ለአሸባሪዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ።በዚህም ዛሬ ሶሪያ በተለይም ጥንታዊቷ ከተማ አሌፖ ፈራርሳ ነዋሪዋቿም የምድር ሲኦል ውስጥ ወድቀዋል።
ግጭቱ ከተፈጠረበት ኤ/አ/አ 2011 እስከ ሜይ 2013 በሁለት ዓመት ብቻ 94 ሺህ ሰዎች መሞታቸውን Syrian Observatory for human rights የተባለ መቀመጫውን ብሪታንያ ያደርገ
ተቋም ገልጿል።ባለፉት 8 ዓመታት የሟቾቹ ቁጥር 400 ሺህ መድረሱን በሶርያ የተባበሩት መንግስታት እና የአረብ ሊግ መልዕክተኛ ይፋ አድርገዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሃገሪቱን አንድነት የጠበቀና ዕልቂትን የቀነሰ ለውጥ እንዴት ይመጣል ብለን ግራ በተጋባንበት አንዲት ጥይት ሳይጮህ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተዓምር ብለን እንዳንጠራው ዛሬ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ አሳዛኝ ክስተቶች የሚያግዱት አይሆንም።ያን አስፈሪ የተባለውን ሁኔታ በእግዚ አብሄር ርዳታ እና በለውጥ ሃይሉ ጥረት የተሻገርን ቢሆንም ዛሬም ኢትዮጵያን ወደ መከራ ሕዝቧንም ወደ ዕልቂት ለመክተት የሚረባረቡ ሃይሎች መኖራቸውን እያየን በመሆኑ ሁላችንም ዕረፉ ልንላቸው ይገባል።ሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖችም የችግሩን አሳሳቢነት እና የአደጋውን ሥፋት ይበልጥ የሚያውቁት በመሆናቸው በተዋረድ ከተኮለኮሉ ብሄርተኞች እና መንደርተኞች መዋቅራቸውን እያጸዱ ካልተጓዙ መንገጫገጩ ይቀጥላል። በመንገጫገጩም ውስጥ ቢሆን በጣም በደማቁ የሚታይ ለውጥ ግን አለ።
መጋቢት 30/2011 ብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ የቀረበ