Saturday, October 26, 2013
Tuesday, August 6, 2013
የጭለማ ቤት ጓደኞቼ
የጭለማ ቤት ጓደኞቼ
ሲሳይ አጌና
ልክ
የዛሬ አምስት ዓመት በጥቅምት 1999 ዓ.ም ዓለም በቃኝ ጭለማ ቤት የነበሩት የጭለማ
ቤት ጓደኞቼ ዛሬ ተመልሰው ጨለማ ቤት ከወደቁ አንድ ወር አስቆጠሩ፤ለመብት
እና ለነጻነት መቆም፣ለእውነት እና ለፍትህ መሰለፍ፣እኩልነት እና ዲሞክራሲ መጠየቅ በወንጀል ተመንዝሮ፣በአሸባሪነት ተፈርጆ ወህኒ
ወርደዋል፤ክሱ የፈጠራ፣ሁሉ ነገር የጨበጣ እንደሆነ ከመነሻው ግልጽ የሆነው የሕወሐት መሪዎች ውሸታሞች መሆናቸው ስለሚታወቅ ብቻ
አልነበረም፤ባለፉት ሃያ ዓመታት የፈጠራ ክስ በማቀነባበር፣አሳፋሪ "ማስረጃ" በመፈብረክ ስለሚታወቁም ብቻ አይደለም፤ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ለመወንጀል
እና ሕዝብንም ለማሸበር ራሳቸው ፈንጂ እያጠመዱ በሀገሪቱ የሽብር ድርጊት መፈጸማቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር (ጉዳይ ፈጻሚ) የነበሩት ቪኪ ሀድልስተን ስላረጋገጡ እንዲሁም የሕወሀት የሽብር ታሪክ በግሎባል
ቴረሪዝም ዳታ ቤዝ ላይ ጭምር ስለተመዘገበ
ነው።(ቪኪሀድልስተን እ/ኤ/አ
አርብ ኦክቶበር 6/2006 ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የላኩትንና ሀሙስ ሴፕቴምበር 1/2011 ዊክሊክስ ይፋ ያደረገውን መሉ መልዕክት በዚሕ ጽሁፍ መጨረሻ ገጽ ላይ ሰፍሯል፤ከምንጩ ለማየት ከፈለጉ
ደግሞ በዚህ ሊንክ ያገኙታል http://www.cablegatesearch.net/cable.php?id=06ADDISABABA2708&q=ethiopia የሕወሐትን የቀደመ የሽብር
ታሪክ ደግሞ
በዚህ ሊንክ ያገኙታል፤http://www.start.umd.edu/gtd/search/Results.aspx?search=Tigray+peoples+liberation+front+%28TPLF%29&sa.x=49&sa.y=20
የሕወሐት ደህንነቶች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ወንጅለው ለማሰር ሲሉ ኑሮን
ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ንጹሃንን ፈንጂ አጥምደው መግደላቸው ነው በዊክሊክስ ሰነድ የተጋለጠው፤በምርጫ 1997 በተመሳሳይ
ተቃዋሚዎችን ለመወንጀል ፖሊሶችን ጭምር በቦምብ
እና በጥይት መግደላቸውን የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል አጋልጠዋል፤በሃይል እና በጠለፋ የሪፖርቱን መደምደሚያ ከልሰው ለፓርላማ ባቀረቡት በእነ ዶ/ር መኮንን ዲሳሳ ሪፖርትም ላይ ሰልፈኞቹ የጦር መሳርያ አለመያዛቸው ተሰምሮበት በፓርላማው
ጸድቋል፤ፖሊሶቹ ደግሞ የተገደሉት በጦር መሳርያ መሆኑ በዚያው ሪፖርት
ላይ ተረጋግጧል።"ተራራውን ያንቀጠቀጠው" እንዲሁም
ባለፉት 20 ዓመታት ሕዝቡን በርሀብ እና በሽብር የቀጠቀጠው ሕወሐት ማለት ይህ ነው።
አንሰበርም
ብለው ለሕዝብ መብት እና ነጻነት የቆሙ ወገኖችን ለመወንጀል ሆቴል እና ታክሲ ላይ ፈንጂ እያጠመዱ ንጹሃንን የሚፈጁ ጨካኞች እያንዳንዱን ሰው ለማሰር አንድ ታክሲ ሙሉ ንጹሃንን ከሚያቃጥሉ የጸረ
ሽብር ሕጉ እንኳን ስራ ላይ ዋለ የምለው ከውስጥ በመነጨ ስሜት ነው፤ይሕ ሕግ ባይኖር ኖሮ አቶ በቀለ ገለታን እና ወጣቱን ፖለቲከኛ
ኦልባና ሌሊሳን አሸባሪ ብሎ ለማሰር ቢያንስ አንድ ታክሲ በፈንጂ ማጋየታቸው የሚጠበቅ ነበር፤ጋሽ ደቤን (አንጋፋውን አርቲስት ደበበ
እሸቱን) ለማሰር አንድ ሆቴል ወይንም ሌላ ታክሲ፣እስክንድር እና አንዱዓለምን ለመክሰስ እንዲሁ ተጨማሪ አውሬያዊ ድርጊት ሊፈጽሙ
ይችሉ እንደነበር ከጀርባ ታሪካቸው በመነሳት መደምደም ይቻላል። ...ወደ ጨለማ ቤት ጓደኞቼ ልመለስ...
ከአምስት
ዓመት በፊት ሀምሌ 20 ቀን 1998 ዓ.ም አንዱ ዓለም አራጌና እስክንድር
ነጋ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ነበሩ፤በዚህ ዕለት ከሰዓት ከቀኑ አስር ሰኣት ገደማ እስክንድር ዞን 5 ከሚባለው ስፍራ ተወሰደ፤አንዱዓለምም
ዞን አንድ ከተባለው የእስር ግቢ እቃህን ጠቅልለህ ውጣ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ደረሰው፤እስክንድር እና አንዱ ዓለም በፖሊስ መኪና
ተጭነው ወደ ቀድሞው ከርቸሌ እስር ቤት ከተወሰዱ በሗላ ዓለም በቃኝ
ጨለማ ቤት ተቆለፈባቸው፤አስቀድሞ ወደ ጨለማ ቤት ተወስዶ የነበረው
ሙሉነህ ኢዩኤልም እንደገና ወደ ጨለማው ተመለሰ፤ትንሽ ሲቆዩ እኔም ደበርኩዋቸውና ነሀሴ 12 ቀን 1998 ከቃሊቲ ወስደው የጨለማው
ቤት ማህበርተኛ አደረጉኝ፤ጓደኞቼ በሞቀ ወሬ ተቀበሉኝ፤እያወራን እኩለ ሌሊትን ተሻገርን፣ሊነጋ ሲል በእንቅልፍ ተሸነፍኩኝ፤ከእንቅልፌ
ነቅቼ ዙሪያውን ሳማትር ግድግዳው በጽሁፍ ተሞልቷል፤"ከዚህ
ሕይወት አንድ ገመድ አይሻልም ወይ ?" የሚለው ሳይደበዝዝ በደማቁ ይታያል፤በብቸኝነት የስቃይ ሕይወት ተማሮ ገመድ የተመኘውና ገመድም አጥቶ ምኞቱን እዚያ ጭለማ ቤት ትቶ ተራውን ለኛ
የለቀቀው ማን እንደሆነ አላወቅንም፤ዘግይቶ በደረሰን መረጃ እዚያ ክፍል ውስጥ የነበሩት ሻለቃ ጸሃዬ ወልደስላሴ ነበሩ፤ሻለቃ ጸሀዬ ወልደስላሴ ሕወሐትን በአፍላው ዘመን በ1968
ተቀላቀሉ፣እስከ ግንቦት 4 ቀን 1994 ከሕወሀት ጋር ቀጠሉ። (መከላካያ ሰራዊቱ ከፖለቲካ ነጻ የሚሆነው ወረቀት ላይ ብቻ መሆኑ ይታወቃል)
ሻለቃ
ጸሃዬ በየካቲት ወር 1993 ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሐት) ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ የስብሰባውን መሪና የደህነነት ሚኒስትሩን አቶ ከንፈ ገ/መድህን በጥይት ገድለዋል በሚል ታሰሩ
፤ ሻለቃ ጸሀዬ በቅድሚያ በማዕከላዊ ምርመራ ፣በሗላም በዓለም በቃኝ
፣በመጨረሻም በቃሊቲ ከ 6 ዓመታት በላይ ጨለማ ቤት አሳልፈዋል፤እኚህ
ሰው ከግንቦት 4 ቀን 1993 እስከተገደሉበት ቀን ድረስ 6 ዓመት ከ2 ወር ከ26 ቀን የታሰሩት ለብቻቸው ነበር፤...ሃምሌ 29 ቀን
1999 ሌሊት የቃሊቲ እስር ቤት ሃላፊዎች ሻለቃ ጸሀዬ መኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ "ሻለቃ ጸሐዬ ስለታመመ መጥተሽ
እዪው " በማለት ባለቤታቸውን ይዘዋቸው ይሄዳሉ፤ሴትየዋ
ዛሬ ወደማያስታውሱት አንድ ግቢ አስገብተው ወደ አንድ ክፍል እያመላከቱ "እዚያ ክፍል ተኝቷል፤ግቢና አነጋግሪው"
ብለው ይመርዋቸዋል፤ባለቤታቸውን ሻለቃ ጸሀዬን ሊያነጋግሩ የገቡት ወይዘሮ የጠበቃቸው
በደም የጨቀየ የባለቤታቸው አስክሬን ነበር፤ሕወሐት እንዲህም ነው።
ስለጨለማ
ቤት ጉዋደኞቼ ሳነሳ የጨለማ ቤቱ ግድግዳ ፊቴ ላይ ተደቅኖ ብዙ ርቀት ወሰደኝ፤በዘረኝነት እያበዱ ከነቁሻሻው ሕወሐትን የሚደግፉ፣ሺህ
ዘመን እሱ ይግዛን በማለት ለአቶ መለስ ውዳሴ የሚያቀርቡ (በቨርጂኒያ አርሊንግተን የነበረውን
ውዳሴ እና ጭፈራ ልብ ይሏል፤ በዚህ ሊንክ ያገኙታል፤ http://www.youtube.com/watch?v=XW5jvUV2T04) ሕወሀት እና አቶ መለስ
ከዘረኝነታቸው ባሻገር ጭካኔያቸው በርሃ ወርደው በመከራ ውስጥ ባለፉት ላይ ጭምር መሆኑ የሚከሰትላቸው መቼ ይሆን? ወይንስ ሻለቃ
ጸሀዬ ዘራቸው ሲቆጠር ሌላ ሆኖ ተገኘ? በሻለቃ ጸሃዬ የተገደሉት
የአቶ ክንፈ ገብረመድህን ደም ደመ ከልብ ይሁን እያልኩ አይደለም፤አቶ ክንፈን የገደለ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከገደለ ወንጀለኛ
በተለየ ለምን ሰቆቃ ይፈጸምበታል? ነው ጥያቄው።ገዳይም፣ሟችም የታገሉለት
ሥርዓት በኢትዮጵያ ምድር ጥላቻ እና ሰቆቃ ያነገሰ፣ዕኩልነትን የገሰሰ መሆኑ ጸሃይ በወጉ ያገኘው ዕውነታ ቢሆንም፣ሰብኣዊና
ሕጋዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት አምናለሁ።
በኢህአዴግ
የ20 ዓመታት አገዛዝ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው አስረኞች በተረጋገጠ
መረጃ ሁለት ብቻ ሲሆኑ፣እነርሱም ጄኔራል ሃየሎም አርአያን የገደለው ጀሚል ያሲን እና አቶ ክንፈን የገደሉት ሻለቃ ጸሀዬ ወልደስላሴ
ናቸው፤ሌሎች ሁለት እና ሶስት ሰው ገድለው ሞት የተፈረደባቸው በርካታ ሰዎች በወህኒ ቤት ውሰጥ ሲኖሩ፣አንዳንዶቹ ሞት ፍርዱ ከጸናባቸው
17 ዓመታት አልፏቸዋል፤ሁሉም ሰዎች እኩል ቢሆኑም ሕወሐቶች የበለጠ እኩል ናቸው እና የሆነው ሁሉ መሆን የሚገባው ነበር።በነገራችን
ላይ በሌሎቹ ላይ ለምን ሞቱ ተፈጻሚ አልሆነም እያልኩ ሳይሆን፣የሕወሐት መዝገበ ቃላት ሰው የሚለውን ቃል
ሕወሐት በሚል የሚፈታው መሆኑን ለማሳየት ብቻ
ነው፤እርግጥ ነው ሻለቃ ጸሃዬ ለ6 ዓመታት ከሰው ሳይገናኙ የውስጣቸውን በውስጣቸው እንደያዙ መገደላቸው ከግድያው ጀርባ ማን አለ?የሚለውን
ጥያቄ በብርቱ ያስነሳል፤አቶ ክንፈ የተገደሉበትን ስብሰባ ሊመሩ ከመነሻው ፕሮግራም የተያዘላቸው አቶ መለስ ዜናዊ አቶ ክንፈን ልከው ርሳቸው መቅረታቸው የአጋጣሚ ተብሎ እንዳይታለፍ ሻለቃ
ጸሃዬ ከሰው ሳይገናኙ 6 ኣመታት በጨለማ ማሳለፋቸው እንዲሁም የሚሊኒየሙ
ይቅርታ በታወጀበት፣የቅንጅት መሪዎች በተፈቱ በ17 ኛው ቀን መገደላቸው አብዝተን እንድንጠረጥር ጠልቀን እንድንመረምር የሚያደርግ
ነው፤ለህወሀት ቅርብ የሆኑ ሰዎች ሴራ አለ የሚለውን ቢያጣጥሉም።....
አልፎ አልፎ
የምጽፋቸውን ጽሁፎች የተመለከተ አንድ ታዛቢ የተለያዩ ርዕሶችን አንድ ላይ አትደርት ለየብቻቸው ጻፋቸው ያለኝ ትዝ ስላለኝ ርዕሴ ሕወሀት እና ሻለቃ ጸሀዬ ከመሆኑ በፊት ልመለስ፤ ...አዎን ሻለቃ ጸሃዬ የነበሩበትን ጨለማ
ቤት ዛሬ ተመልሰው ጨለማ ከተጣሉት እስክንድር እና አንዱዓለም እንዲሁም ዛሬ በውጭ ከሚኖረው ሙሉነህ ኢዩኤል ጋር በ1998 ክረምት ተረከብን፤ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ በ17 የማጭበርበር ወንጀል ተከሶ ከወህኒ
ቤት ያመለጠ ወርቁ የተባለ ሰው ሲያዝ ጨለማውን ለሱ ለቀን ለእኛ ቆርቆሮ ቤት ተቀለሰልን፤አንድ የኮንፈረንስ ጠረጴዛ የምታህል ግቢም
ታጠረልን፤ዓለም በቃኝ ወህኒ ቤት ያረፈበት ስፍራ ለአፍሪካ ሕብረት
አስቀድሞ በመሰጠቱ ሕብረቱ ግንባታውን ሲጀምር በህዳር ወር 1999 ከጠባቡ ወህኒ ቤት ወደቃሊቲ ተጭነን ከሌሎች አባሪዎቻችን
ጋር ተቀላቀልን፤ከወራት በሗላ ሁላችንም ወደ ሰፊው እስር ቤት ተለቀቅን፤በተፈታን በአምስተኛው ዓመት እስክንድር እና አንዱአለም
አሸባሪ የሚል ስም ወጥቶላቸው እንደገና ወደ ጨለማ ቤት ተመለሱ፤ከነርሱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ታዋቂው የቲያትር ባለሙያ እና ፖለቲከኛ አርቲስት ደበበ እሸቱ
በ70 ዓመቱ በአሸባሪነት ታሰረ።
ጋሽ ደበበ እንዲሁም በህዳር 1999 በአፍሪካ ሕብረት ሳቢያ ከጠባቡዋ እስር ቤት የወጡት አንዱዓለም እና እስክንድር
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ሚኖርበት የቁም እስር የተሸጋገሩት ወይንም
ከቃሊቲ የወጡት ሽምግልና እና ይቅርታ የሚል ኮተት ቢንጠለጠልለትም
እውነታው እና በዊክሊክስ ሰነድ በዲፕሎማሲያዊ ቃና እንደተረጋገጠውም
በአሜሪካ መንግስት ግፊት ነበር፤እንዲያውም እስክንድር ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ በነጻ የተለቀቀ ቢሆንም፣የመንግስት መገናኛ ብዙሃን
በተያዘ እለት ምሽት በይቅርታ ነው የወጣው በማለት ዘግበዋል፤ሁሉ ነገረ በደመነፍስ ስለሆነ የእስክንድር እና አንዱዓለምን እንዲሁም የጋሽ ደበበን፣የአቶ በቀለ ገለታን፣የአቶ
ኦልባና ሌሊሳን፣የነክንፈሚካል ደበበን ወዘተ አሸባሪነት የሚያስረዳ በቶን የሚቆጠር መረጃ እንዳላቸው ሰሞኑን አቶ መለስ የዓመቱን ዕቅድ ለፓርላማ ሲያቀርቡ እንሰማለን፤ለመዋዕላ ሕጻናት የማይመጥን
የመከነው ሽብር ወይንም ሌላ ስም የሚሰጡት
ቲያትር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እናያለን።...አርቲስት ደበበ እሸቱ፣.አንዱዓለም እና እስክንድር ከግንቦት 7 የተቀበሉት መመሪያ እና
ለአሜሪካ ወይንም ለእንግሊዝ መንግስት፣ምናልባትም ለኤርትራ የስለላ ተግባር ሲያከናውኑ እንደነበር የሚያስረዳ በጌታቸው አሰፋ ወይንም
በኢሳይያስ ወልደጊዮርጊስ የተደረሰ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሚተረክ ፎርጀሪ እና ቀሽም ዶክመንተሪ በነጻ ያሳዩናል፤ለተመልካቹ
ሳይከፍሉ ለማለት ነው።
የኢትዮጵያ
ቴሌቪዥንን አዘውትሮ ማየት አይኪው ዝቅ ያደርጋል ይል ነበር እስክንድር።በርግጥም ሆድ በርሃብ እየጮኸ፣ሕሊና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
እየተራቆተ ደስታ እንደራቀን ስቃዩ የሚቀጥለው እስከመቼ ይሆን? በርግጥ ደልቷቸው የሚስቁ፣ባርነት ተመችቷቸው የሚገለፍጡም አልታጡም፤መቼም በባርነት ስር ሆኖ የሚደሰት አዕምሮው ማፍሰስ
የጀመረ እንጂ ሙሉ ጤነኛ ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፤ሳቅ ሲነሳ ከዓመት በፊት የነበረው የእስክንድር የሳቅ ምኞት ታወሰኝ፤ ቦሌ መንገድ
ዓለም ሕንጻ ከሚገኘው ላፓሬዚያን ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ማኪያቶ እንጠጣለን፤ያው እንደ ሁሌው ፖለቲካውን ስንሰልቅ ከአጠገባችን ያሉት ጎረምሶች በሳቅ ያውካካሉ፤አንዳንዶቹ
ከምር በሳቅ እየፈረሱ ነበር፤ጨዋታቸው የደራ ነውና ትኩረታችንን ስበዋል፤. "እኛ መቼ ነው የምንስቀው ?"
በሚል እስክንድር ለወረወረው ሃሳብ
በወቅቱ ምላሽ አልነበረኝም፤ ግን አንዳንዴ ሳስበው የሚታኘክ በሌለበት፣ደስታ በጠፋበት ጥርስ ራሱ
በኢትዮጵያ ምን ያደርጋል? ...
ሳቅ እየናፈቀው ጨለማ ቤት የሚንከራተተው እስክንድር ነጋ የወርቅ ማንኪያ ጎርሰው ከተወለዱ
የሃብታም ልጆች አንዱ ነው፤የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የጀመረው ዛሬ የአቶ መለስ ልጆች በሚማሩበት እንግሊዝ ስኩል
ሲሆን፣የሁለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው በዩ.ኤስ አሜሪካ ነበር፤በዚህ ሂደት ያለፉ ሰዎች (ያ ትውልድን አይጨምርም) በአብዛኛው ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ግኑኝነት የላላ እንደሆነ በስፋት ሲታመን፣እንደ
ኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ መግባት በእነሱ ዓይን የጤንነት ምልክት ተደርጎ የሚታይ አይደለም፤የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት
ሲፈነዳ የቦሌ ልጆች "እኛ ምን አገባን የጨርቆስ ፣የፈረንሳይ እና የሽሮሜዳ ልጆች ይቸገሩበት " አሉ ተብሎ
እንደተቀለደው ወደ እስር ቤት መወርወር እና መከራ መቀበል እንደኛ
የኔታጋ ፊደል ቆጥረው አምሃ ደስታ እና መሰል የመንግስት ት/ቤት ለተማሩ እንጂ በርግጥም በእንግሊዝ ስኩል
ላለፉ ከባድ ቢሆንም፣እስክንድር በአቶ መለስ የ20 ዓመታት አገዛዝ ለ8ኛ ግዜ እስር ቤት ገብቷል፤ጨለማ ቤትም ተጥሏል።
በጥቅምት
1985 የፕሬስ ነጻነት መታወጁን ተከትሎ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ኢትዮጲስ ጋዜጣን በማቋቋም ከሟቹ ታዋቂ ጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ጋር በነጻ ፕሬስ ውስጥ የሚታይ ደማቅ
አሻራ አሳርፏል፤በመቀጠል ሀበሻ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ፣በሗላም ምኒሊክን ጨምሮ ሶስት ጋዜጦችን በማቋቋም እስከ ጥቅምት 1998 ሲሰራ ቆይቷል፤ምርጫ
97ትን ተከትሎ በህዳር 1998 ለ 7ኛ ግዜ ወደ እስር ቤት ተወሰደ፤አሁን ለ8ኛ ግዜ። በዚህ ሂደት በተለይም በ1988ቱ እስራት ወቅት ባዶ ክፍል ቀዝቃዛ ወለል ላይ እንዲተኛ በማድረግ እንዲሁም
በተፈጸመበት ድብደባ በእጁ ላይ ውልቃት ደርሶበታል፤አሁንም የችግሩ
ሰለባ እንደሆነ ቀጥሏል።በ1998 እስክንድርን ለማሰር ስሙ በጋዜጣ አዘጋጅነት ስላልሰፈረ እንዲሁም በባለቤትነትም እንዳይጠይቁት
ምንም ቀዳዳ ሲያጡ ጨርሶ አባል ባልሆነበት የቅንጅት አመራር በማለት ከሰሱት፤አንድ ዓመት ከ6 ወር ታስሮ በነጻ ተለቀቀ፤በጋዜጣ
ስራም እንዳይሰማራ በፖለቲካ ውሳኔ ታገደ።
የሕወሐት መሪዎች
ያኔም ዛሬም እስክንድር ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግኑኝነት እንደሌለው ያውቃሉ፤አሁን በግንቦት 7 ፈርጀውት በአሸባሪነት ሲከሱትም ከግንቦት 7 ጋር
ግኑኝነት አለው ብለው በማመን ሳይሆን፣በኢንተርኔት እና በሀገር ቤት አንዳንድ ጋዜጦች ላይ የሚጽፈው ዕውነት ስላንገሸገሻቸው፣ትንተናው
ስላባነናቸው ብቻ ነው፤.የአሁኑ እስራት የቅንጅት መሪዎች በተፈቱበት ወቅት አቶ መለስ ለሕወሐት ሰዎች ተናገሩ የተባለውን ያስታውሰናል፤በምዕራባውያኑ
የተደረገውን ግፊት ተከትሎ የቅንጅት መሪዎችን ለመፍታት እና በፖለቲካው ሂደት እንዲቀጥሉ የሕወሀት አመራር ሲወስን፣የፖለቲካው አካሄድ
የማይገባቸው የሕወሀት ጄኔራሎችና ሌሎች ሕወሐቶች አኩርፈው ነበር አሉ፤ አቶ መለስ ለነርሱ የሰጡት ማጽናኛ "አታስቡ
እግር እስኪያወጡ እንጠብቃቸዋለን፤ሊራመዱ ሲሉ እግራቸውን እንቆርጠዋለን" የሚል ነበር ፤ከሕወሀት ውጭ ያለውን
አንድም በአሽከርነት አሊያም አዋርደው ለመግዛት የተነሱት የህወሀት መሪዎች
ሁሉንም ለመስበር ቀና ያለውን መቀንጠስ ያስፈልጋል በሚል የወሰዱት ርምጃ ነው።
የማርቲን
ሉተር ኪንግ አድናቂ፣ሰላማዊ ትግል ላይ የቆረበውንና ባለፉት 12 ዓመታት በዚሁ የትግል መስመር ላይ ጸንቶ የቆመውን አንዱዓለም
አራጌን በአሸባሪነት መክሰስ፣ከሳሾቹ ደግሞ በዓለማቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት
የተመዘገበው የሕወሀት መሪዎች መሆናቸው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም
የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ነው፤አስገራሚው ነገር መንግስት ሆነውም በዚሁ የሽብር ድርጊታቸው መቀጠላቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ ሰነዶች
ባረጋገጡበት እነ አንዱኣለምን በሽብር መክሰስ የሕወሐት የደመነፍስ ጉዞ አሁንም እየተወለካከፈ መቀጠሉን ከማሳየት ውጭ የሚጨምረው
ነገር የለም፤ዛሬ የህወሀትን ውንጀላ የሚያምኑ በዘር ጥብቆ ውስጥ ገብተው ጉድጓድ ውስጥ እንዳለችው እንቁራሪት ሰማዩ የጠበበባቸው
የሕወሀት ሰዎች ብቻ ናቸው።
አንዱዓለም
በ1990 ዎቹ መጀመሪያ በአዲስ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ካውንስል አመራር ነበ ር፣የፖለቲካ ተሳትፎውንም ከ1992 ጀምሮ በፓርቲ በመታቀፍ
ቀጥሏል፤በኢዴፓ ምክትል ጸሐፊነት፣በቅንጅት ለዕላይ ምክር ቤት አባልነት አገልግሏል፤በምርጫ 2002 የፓርቲዎች ክርክር የምርጫውን ሙቀት በመጨመር ብዘዎች ያስታውሱታል፤በዚያ የፓርቲዎች ክርክር
የተናገረው የተቆረጠበት ብቸኛ ተከራካሪም እርሱ ነበር፤አሁን የኢህአዴግ አጋር ፓርቲ አመራር በመሆን በተገቢው ቦታ ላይ የሚገኘው
የኢዴፓው ልደቱ አያሌውን በተመለከተ የተናገረው እንዲሁም ሬድዋን
ሁሴን የተባለ ኢህአዴግን በወዶገብነት የተቀላቀለ ግለሰብ ከተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግ ያደረገውን ሽግግር የተቸበት ክፍል
ተቆርጦ ወጥቷል፤ቃሊቲ እስር ቤትን ከደቡብ አፍሪካው ሮቢን አይላንድ ጋር በማነጻጸር የቃሊቲን ሲኦልነት የገለጸበትም እንዳይተላለፍ
ታግዷል፤ምርጫ 1997ትን ተከትሎ በተወሰደው የእስራት ርምጃ አንዱኣለም እስር ቤት ቤት ብቻ ሳይሆን ጨለማ ቤት ተጥሏል፤ከጨለማ በተጨማሪ አደገኛ ቦዘኔ
ዞን በተባለው የእስር ሰፍራ ተወስዶ የታስረ ብቸኛ የቅንጅት እስረኛ ነበር፤የቅንጅት መሪዎች የፈረሙበትን የይቅርታ
ወረቀት አንፈርምም ብለው ካንገራገሩትም አንዱ አንዱዓለም ነው፤...ለፈው እንግልት አልበቃ ብሎ ከሁለት ሕጻናት ልጆቹ ሩሕ እና
እጹብ ነጥለው መልሰው ጨለማ ውስጥ ጥለውታል፤እስክንድርንም እስር ቤት ከተወለደው የ 5 ዓመት ሕጻን ልጁ
ናፍቆት ነጥለው ነበር በሰንሰለት አስረው የወሰዱት።
ሽብር
ሲነሳ ዓለም አልቃይዳን እና ቢንላደንን በዋናነት ያስታውሳል፤ሕወሐት ደግሞ
ኦነግ እና ኦብነግን ይጠቅሳል፤አሁን ደግሞ ግንቦት 7 ተጨምሮበታል፤እድሜ ለዊክሊክስ እና ለግሎባል ቴረሪዝም
ዳታቤዝ በሽፍትነቱም፣በመንግስትነቱም አሸባሪው ሕወሐት መሆኑን አጋልጠዋል፤
የዊክሊክስ ምስጢራዊ ሰነዶች የህወሐትን መንግስታዊ አሸባሪነት ከማጋለጥ ባሻገር ብዙዎች በአሜሪካ መንግስት ላይ የነበራቸውን ቅሬታም የገፈፈ ሆኖ አልፏል፤አዲስአበባ ላይ የተፈራረቁት የአሜሪካ አምባሳደሮች
ህወሃት ደጋፊ የሆኑት ቪኪ ሀድልስተንን ጨምሮ ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ
ሁኔታ የጠራ እና የተብራራ ሪፖርት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን እድሜ ለዊክሊክስ
ተረድተናል፤የአንድ ዘር አገዛዝ በሀገሪቱ መስፈኑን፣የሌሎች ሚና የአጫዋችነት መሆኑን በዝርዝር ደጋግመው ጽፈዋል፤ የሕወሐት መሪዎች
ሰዎችን በሀሰት ወንጅለው እንደሚያስሩሌላው ቀርቶ ሰዎችን ለማሰር ሲሉ ፍንዳታ እንደሚያቀነባብሩ እድሜ ለዊክሊክስ ሁሉም ተገለጠ።
እዚህ
ላይ ሌላው በደማቁ የሚሰመርበት ነጥብ በሕወሃት ሰዎችና አደግዳጊዎቻቸው
አቶ መለስ ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ አላቸው በሚል ሲለቀቅ
የነበረው ነጠላ ዜማ ወደ ተረተትነት መቀየሩ ነው፤ዲፕሎማቶቹ በአቶ
መለስ ንግግር ያመኑ መስለው በአደባባይ እየለፈፉ፣እየተየቡ የሚልኩት
ሌላ መሆኑ በቂ ብርሃን አግኝቷል፤የአቶ መለስ የንግግር
ችሎታ የማይካድ ቢሆንም፣ ብዙ ግዜ የማሳመኛ ነጥባቸው ወይንም መከራከሪያቸው የይሉኝታ ገደብን ያለፈ፣በስድብ የታጀበ እንደሆነም በግልጽ ይታወቃል፤በጄኔቭ የአሜሪካ
አምባሳደር ዳግላስ ግሪፍዝስ በኢትዮጵያ የአንድ ዘር የበላይነት ስለመግነኑ በማንሳት፣ይህም ችግር ያስከትላል በማለት
በሰብዓዊ መበት ኮሚሽን ጉባኤ ላይ የዛሬ 3 ዓመት ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፤ይህንን በተመለከተ በታህሳስ 2001 በሰጡት
ጋዜጣዊ መግለጫ የተጠየቁት አቶ መለስ ዜናዊ ዕውነታውን ከመካድ ባሻገር አሜሪካዊውን ዲፕሎማት ደደብ ማለታቸው በአደባባይ የተነገረ
ነውና ብዙዎች ያስታውሱታል፤ ገሃዱን ዕውነታ በስድብ ለማስተባበል መፍጨርጨር፣ይህ ግፍና ውርደት ከዚህ በላይ ለማስቀጠል መታበይ
አጸፋው የውርደት ውርደት እንደሚሆን ቀኑን አንወቀው እንጂ ሳይታለም የተፈታ ነው፤መውደቃችሁን የሚጠራጠር እርሱ ሕሊናው የዘረኝነት
ሞራ የለበሰ፣እንዲሁም በጥቅም አብዶ አዕምሮው ያፈሰሰ ብቻ ነው፤ሌላው እንዳትወድቁበት ይጠነቀቃል እንጂ ሩቅ በማይባል ግዜ መውደቃችሁን
አይጠራጠርም።የአፍሪካ ንጉሰ ነገስትነትን ሲያልሙ ሲርቲ ጉድጓድ የወደቁትን ጋዳፊን ያየ በስልጣን ይጫወታልን?ለመሆኑ የአቶ መለስ ሲርቲ የት ይሆን? አድዋ ወይንስ ቻይና?
እነሆ አድራሻዬ፦ lualawi2000@yahoo.com
ጥቅምት
6/2004
Subscribe to:
Posts (Atom)