Wednesday, May 19, 2021

የማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች እና ለትናንት ያላቸው ፍቅር

የማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች መግለጫ እና ለትናንት ያላቸው ፍቅር !
                                                                            ሲሳይ አጌና 
       የማህበረ ቅዱሳን አመራሮች  በማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን በቅርቡ ስላወጡት  መግለጫ  የሰጡትን ማብራርያ የተከታተልኩት ዘግይቼ ነው።ስለ መግለጫው  የቀድሞ አመራሮች (ከአንዱ በቀር) ማብራርያ የሰጡበት  እና ሌሎቹ ያልተገኙበት ምክንያት ግን አልተገለፀልንም።(ክፍል 1 እና ክፍል 2 ይመልከቱ) የማህበሩ ሰብሳቢ  አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ  እና የቀድሞ አመራሮች  ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ እና ዲያቆን ብርሃኑ አድማሴ መግለጫ የሰጡት በቅርቡ ያወጡትን አነጋጋሪ መግለጫ በተመለከተ  እንደሆነም ግልጽ አድርገዋል። 
     የማህበሩ አመራሮች ከሰብሳቢው ውጭ ያሉት ያልተገኙበት እና የቀድሞዎቹ ምላሽ  የሰጡበት ምክንያት መግለጫውን የአሁኑ አመራር ብቻ ሳይሆን እኛም እናምንበታለን የሚል የአጋርነት መግለጫ  ወይንም ተባባሪነት  ሊሆን ይችላል።ወይንም መልዕክቱን ይበልጥ መስደድ  የተፈለገበት አካባቢን ታሳቢ አድርጎም ሊሆን ይችላል።ምንም ይሁን ምን ለጉዳዩ ማብራርያ መስጠታቸው ይበልጥ ነገሮችን ግልፅ አድርጓል። 
 መልዕክታቸውን ሳትረዱ ለትችት ቸኮላችሁ የሚል አስተያየት ለሰጡ ወገኖች የማህበሩ አመራሮች ከተፃፈው በላይ ከባድ  መልዕክት እና  ጠንካራ ተቃውሞ   እንዳላቸው  አሳይተዋቸዋል።ይህንን መልዕክት ሰምቼ  በዝምታ ማለፍ በፍፁም ስላልቻልኩ የሚከተለውን አስተያየትና ጥያቄ አቀርባለሁ።
    ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መከራ የቀጠለ ቢሆንም፣በማህበረ ቅዱሳን መግለጫ  እነደተመለከተው ግን በምንም መመዘኛ   ቤተክርስቲያኒቱ ከትናንቱ  የከፋ  አደጋ  አልተደቀነባትም። ሆኖም ምናልባት  አደባባይ ያልወጡ እነሱ እና የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ብቻ የሚያውቋቸው አደጋዎች ይኖሩ ይሆን?  ምናልባት ከዚህ ቀደም በሕወሃት ዘመን እንደነበረው በአቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት እንደሚያደርገው ሁሉ ዛሬም ቤተክርስቲያኒቱ  በአቶ ተመስገን ጥሩነህ ወይንም በሌላ የደህነነት ባላስልጣን ቁጥጥር ሥር ነችን?ሌሎች ያላየናቸው እና  ያልሰማናቸው ቤተክርስቲያኒቱ የተጋፈጠችው ፈተና ፣ምዕመናን የተደቀነባቸው አደጋ አለን? እንደሰማኋቸው ግን  ከምናውቀውና ከሰማነው በላይ የነገሩን ምንም የተለየ አደጋ የለም።ይልቁንም መግለጫውን ባጮሁት ልክ የሚዘረዝሩት አደጋ  ማቅረብ ሲቸግራቸው  ቤተክርስቲያኒቱን የማዳከም ሴራ አለ የሚል ፍንጭ እንኳን ያልቀረበበት ተጨባጭነት የሌለው መላምት ሰንዝረዋል።የአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ማህበር መሪዎች ማህበራዊ ሚዲያ  ላይ  የሚራገብ  እና ማሰብ ለሚችል ሰው የማይመጥን ሸቀጥ ይዘው አደባባይ መውጣታቸው እነርሱ ፈቅድው የገቡበት ቢሆንም  ማህበሩን ግን  በፍፁም አይመጥንም።"አዲሲቱ ኢትዮጵያ የሚባለው ቤተክርስቲያኒቱን ለማደካም" ነው የሚል መጠየቅ ለሚችሉ እና  ከህሊናቸው ጋር ለሚኖሩ የሚያስገምት  ትንተና መስጠትም ከበስተጀርባው ምን ይዟል የሚል ጥያቄም ያስነሳል።
     በዘር ፖለቲካ ስትታመስ፥በአምባገነን አገዛዝ ስትቀጠቀጥ የኖረች እና የዕምነት ተቋማት የተዋረዱባት ሃገር  ከዚህ አዙሪት እንድትወጣ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሎ መመኘትና ለዚያ መስራት ያስከብራል እንጂ ያስወቅሳልን ? ባይሆን በተግባር እንዲፈፀም ማበረታታትና ሥርዓቱ ወደ ትናንት እንዳይመለስ መታገል ያስፈልጋል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስንም ሆነ ሌሎች የዕምነት ተቋማትን ማጠናከር ወደ አውሬነት የተለወጡ ወጣቶችን በመመለስ፤ ሞራልና ሥነምግባር  ያለው ፥ሃገር የሚረከብ ትውልድ  እንዲያብብ  የሚያደርግ በመሆኑ  የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስንም ሆነ ሌሎችን ዕምነት  ላጥፋ  ብሎ በራሱ ላይ  ጥፋት የሚያውጅ ኢትዮጵያዊ መንግስት ይኖራል  ተብሎ አይታመንም። የኢትዮጵያ መንግስት እና ኢትዮጵያዊ  መንግስት ልዩነቱ ግልፅ ይመስለኛል።ጫፍ የሌለው የፌስ ቡክ ወሬ  በተከበረ ማህበር ስም ማስተጋባት ማህበሩን አይመጥንም።
      ግን ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተክርስቲያን ያ ሁሉ መዓት ሲወርድባት የትነበራችሁ? ብዬ አልጠይቅም።መፍራት ወይንም ቤተክርስቲያኒቱ እየተጎዳችም ቢሆን ቅዝምዝሙን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ  እንደ ግለሰቦች ጥንካሬ እና መንፈሳዊነት መጠን ስለሚወሰን መፍራት ቢያስወቅስ እንኳን ወንጀል አይደለም እና እንለፈው።ያልገባኝ ግን   የዛሬውን የቤተክርስቲያኒቱ ችግር  እንዲህ የሚያንገበግባቸው  ወገኖች፣ የትናንቱን የሚታየውን እና የሚዳሰሰውን የሕወሐት ዘመን  ጨለማ  በአፈ ታሪክ የሰማነው ይመስል  ሊክዱት ወይንም ሊያደበዝዙት የፈለጉበት ምክንያት በፍፁም ሊገባኝ አይችልም።ምናልባት በቅንነት ካየነው በዚያ ድቅድቅ ጨለማ የት ነበራችሁ? የሚለውን ጥያቄ ለመሸሽ ሊሆን ይችላል።ነገሩ ግን  በቅንነት አይመስልም። ሁለት የተከፈለችው ቤተክርስቲያን አንድ የሆነቸው፣የተሰደዱትም ፓትርያርክ  ብጹዕ አብነ መርቆርዮስ የተመለሱት  በለውጡ ስለመሆኑ ለተነሳው አስተያየት የሰጡትን መልስ ስሰማ ጉድዩ ከቤተክርስቲያን ባሻገር ነውን ? የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል።”ፓትርያርኩን ያባረረውም ፣ የመለሰውም  ራሱ   ኢህአዴግ  ነው”  የሚል  ዕውነት ላይ  የጨፈነ ምላሽ  መንፈሳዊ ማህበር  ከሚመሩ ሰዎች አይጠበቅም.።
    ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና  ከለውጡ ወዲህ  ያለውን መንግስት ኢሕአዴግ (ለ) ፣ ሟቹን ኢሕአዴግ (ሀ) እያሉ የሚጠሩት ዕውነቱ  ጠፍቷቸው ሳይሆን ፣ በገዢው ፓርቲ ላይ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር መሆኑ ግልፅ ይመስለኛል።አንዳንዶች ይህቺን በግንዛቤ ዕጦት ሲያነበንቧት ፣የግንዛቤ ችግር የሌለባቸው እና  ፖለቲካኛ የሆኑ  ግን  ለፖለቲካ ፍላጎታቸው ሲሉ  ሲያስተጋቡት አድምጠናል።የግንዛቤ ችግር  ሳይኖርባቸው  እንዲሁም  ፖለቲኛም ሳይሆኑ  የሕወሃትን አገዛዝ  ከብልፅግና ጋር አንድ አድርገው የሚመለከቱ የማህበረ ቅዱሳን አመራሮችን  የመሳሰሉ ግን ምን እንደሚባሉ   አላውቅም።
      ማንም ማመዛዘን የሚችል ሰው እንደሚረዳው  ትናንት የነበረው የሕወሓት አገዛዝ ሲሆን፥ ዛሬ ደግሞ ያለው ሕወሃትን ከስልጣን አባሮ ፣ፓርቲውን አሸባሪ ብሎ የፈረጀ የብልፅግና ፓርቲ ነው።ሩብ ክፍለ ዘመን የተከፈለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነቷን ያገኘችው እና ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ በክብር ሃገራቸውን የረገጡት እና ወደ መንበራቸው የተመለሱት  ሕወሃት ከቤተመንግስት በመውጣቱ  መሆኑ ለሚያይ ሁሉ በብርሃን ላይ የተሰጣ ዕውነት ነው።
      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን  በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን የደረሰባትን መከራ እና ሰቆቃ ፣የጅምላ ፍጅት እና ካሕናት አይናቸው ታስሮ ወደ ገደል የተጣሉበትን አሰቃቂ ትዕይንት ከዛሬው ይሻላል ብለው የማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች ሲከራከሩ ሳይ  ማመን ነው ያቃተኝ። ያኔ ስላልነበሩ ወይንም  ስለሚፈሩ  ባይከታተሉት እንኳን ፥ ትናንት ቤተክርስቲያኒቱ ያሳለፈችውንና የተመዘገበውን ሰቆቃ እንደምን ማገላበጥ አቃታቸው? ትናንት በቤተክርስቲያኒቱ እና ምዕመናኑ ላይ የሚፈፀመው  ሰቆቃ የሚመዘገበው በግል ጋዜጦች  ፣በሰብዓዊ  መብት ድርጅቱ ኢሰመጉ እና በፖለቲካ ድርጅት ልሳናት ስለነበር በወቅቱ ላይመለከቱት ይችላሉ።ይህንን እንድል ያስደፈረኝ የማሕበረ ቅዱሳን አመራር የነበሩ ሰው ከለውጡ በፊት  ግዮን መፅሄት ላይ ባሰፈሩት እና በኋላም በኢንተርኔት በተሰራጨው  ፅሁፋቸው  እንደገለፁት የማህበረ ቅዱሳን አመራሮች  የግል ጋዜጦችን ማህበሩ እንዳይገዛ  ይከላከሉ ነበር።ለዚህም የሚሰጡት  ምክንያት መንግስት ማህበሩን ለማፍረስ ሰበብ ያገኛል የሚል ነው። ከዚህ ስንነሳ ምናልባት   የትናንቱ ድቅድቅ ጨለማ ያልታያቸው ማህበሩ እንዳይፈርስ የሚፈፀመውን  ላለማየት እና ላለመስማት በመወሰናቸው አሊያም ምናልባትም  ብዙሃኑ በጥቂቶች ፍላጎት ውስጥ በመውደቃቸው ሊሆን ይችላል።ሆኖም ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀውን ውይይት ሳደምጥ ከመረጃ ክፍተቱ ይልቅ ሥልጣን ላይ ባለው  መንግስት ላይ ያላቸው ከፍተኛ  ጥላቻ  የትናንቱን እንዳያያቱ የጋረዳቸው ይመስለኛል።ምናልባትም የሕወሓት ሥርዓት በመወገዱ  ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ  የሃገሪቱን ከተሞች በደስታ ሰልፍ ሲያጥለቀልቅ ፣እነርሱ  ካልተደሰቱት ወይንም ካዘኑና ከተቆጩት  ውስጥም ሊሆኑ ይችላሉ፥ዘመንፈስን ጨምሮ ማለቴ ነው።
   
     ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ችግር  የሕወሃትን የጭለማ ዘመን ከመጥቀስ ይልቅ ወደ ኋላ 50 ዓመት መሄዳቸው ይበልጥ የገባኝ ቃለምልልሱን ከተከታተልኩ በኋላ ነው። ከንጉስ ኃ/ሥላሴ መንግስት ፍፃሜ በኋላ የቤተክርስቲያኒቱ ሚና መቀነሱና ዕኩልነት መታወጁ ግልፅ ነው።የደርግ መንግስት ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን አስሮ መግደሉም ይታወቃል።ነገር ግን የወንጌላውያን ቤተክርሲያን መሪ የሆኑትን ቄስ ጉዲና ቱምሳንም በተመሳሳይ አስሮ ገድሏል።ምዕመናን በዕምነታቸው ተለይተው የሚታረዱበት፣አብያተ ክርስቲያናት የሚነዱበት ሁኔታ ግን አልነበረም።
    የሕወሃት አገዛዝ ሲመጣ ደግሞ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን ከመንበራቸው አባሮ፣በአቡነ ጳውሎስ የተካበት፥አርሲ አርባ ጉጉ የጀመረ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ውድመት፣የምዕመናን ዕልቂት 27ቱንም ዓመት በዙር  አሰቃቂ በሆነ መንገድ የቀጠለበት እና አያሌ ሺዎች  የረገፉበት ነበር ።በማናቸውም መመዘኛ ቢታይ  በቅርብ ታሪካችን  እንደ ሕወሃት ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  ብርቱ ፈተና አልገጠማትም። 
    የአሰቦት ገዳም 16  መነኩሴዎች አይናቸው  ታስሮ  ጥይት እየተተኮሰባቸው ወደ ገደል እየተነዱ ያለቁት በሕወሃት ዘመን ነው።የፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን ከሥልጣን መነሳትን ተቃውማችኋል በሚል ጳጉሜ 1/1985 በቁጥር 18 የሚሆኑ የጎንደር ኢየሱስ ካህናት እና ምዕመናን  በቤተክርስቲያናቸው ቅጥር  ግቢ  የተጨፈጨፉትም በሕወሃት ዘመን ነው።ጥር 17 /1989  ዓ/ም ባህታዊ ፈቃደ  ሥላሴ በአዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን  ታቦተ ሕጉ በቆመበት በጥይት የተገደሉት በሕወሃት ዘመን ነው።የቤተክርስቲያናችንን ሙዳየ ምፅዋት አናዘርፍም ያሉ የልደታ ቤተክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን በአዲስ አበባ ከተማ የፌደራል ፖሊስ  ጥይት  የዘነበባቸው  እና ቢያንስ አንድ ስንታየሁ የተባለ ወጣት የተገደለውና ሌሎች ወደ ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ የተጫኑትም በሕወሓት ዘመን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ከ5 ኪሎ እስከ ላፍቶ መኖሪያ ቤታቸው በሕወሐት ደህንነቶች በራቸው እየተደበደበ ጥቃት የተፈፀመባቸው በሕወሃት ዘመን በሃምሌ  ወር 2001 ዓ.ም ነበር። በነሃሴ ወር 2004 ዓ/ም አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ለቤተክርስቲያኒቱ ችግር እግዚአብሄር መልስ ሰጠ ብለው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ   አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሃገር እንዲገቡ የፃፉትን  ደብዳቤ እንዲስቡና የቤተክርስቲያንቱ አባቶች ሁለት ቦታ ተከፍለው እንዲቀሩ  እና አዲስ ፓትያርክ አዲስ አባባ እንዲመረጥ የተወሰነው በሕወሃት መሪዎች ነው።
    አስደንጋጭ በሆነ መንገድ የምዕምናን ቁጥር እየቀሰ የሄድውም በሕወሓት ዘመን ነው።የደርግ መንግስት በ1976 ባካሄደው ሕዝብ እና ቤት ቆጠራ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 38 ሚሊዮን 203 ሺህ 681  የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጠው ወይንም   54.2 በመቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሲያን አማኞች ነበሩ።ሕወሃት ሥልጣን በያዘ  3ኛው ዓመት በ1987  በተካሄደ ቆጠራ የኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  አማኞች ቁጥር   ወደ 4 በመቶ ወርዶ 50.6 በመቶ ዝቅ አለ።ከ10 ዓመት በኋላ 
በ1999 በተካሄደ ሕዝብና ቤት ቆጠራ እንደገና 7.3  በመቶ ቀንሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች ቁጥር ወደ 43 .5 በመቶ ወረደ።ለማሕበረ ቅዱሳን መሪዎች  የተሻለ የነበረው  የሕወሓት ዘመን  ለኦርቶዶክሳውያኑ ግን ጭለማ እንደነበር ከብዙ በጥቂቱ የተዘረዘሩት  በግልጽ ይነግሩናል። 
      ሕወሃት ተሽንፎ  ቤተመንግስቱን ለቆ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሲያፈገፍግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድነት ታወጀ።ሩብ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ውሳኔ ተገፍተው የተሰደዱት ፓትርያርክ  አቡነ መርቆርዮስ እና ጳጳሳት ወደ ሃገር ቤት በክብር ገቡ።ዋሺንግተን ዲሲ በተካሄደው የዕርቅ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን  ወደ ዋሺንግተን በበረሩበት አውሮፕላን ይዘው ተመለሱ።ኦርቶዶክስ ሃገር ናት ሲሉም የቤተክርስቲያኒቱን ግዝፈት እና ሚና መሰከሩ።
    እርግጥ ከለውጡም በኋላ ዚጎች  በዕምነታቸውና በብሄራቸው ተለይተው ተገድለዋል።በአሰቃቂ ሁኒታም ታርደዋል። በዘረፋ እና በማውደም የማደሕየት ርምጃዎች መወሰዳቸውም ግልፅ ነው።የድርጊቱ ፈፃሚዎችም በዕምነት እና በብሄር አክራሪነት የተለከፉ የሥርዓቱ ተቃዋሚዎች መሆናቸውም የዚያኑ ያህል ግልፅ ነው።የግፍ ድርጊቱ  ተባባሪዎች ምናልባትም አስፈፃሚዎች ጭምር  በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ተገልፆ ከንቲባዎች፡ አስተዳዳሪዎች እና ሌሎች ባለስልጣናት   ከሥልጣን ተሽረው ወህኒ መወርወራቸውም ይፋ ሆኗል። ከሃጫሉ ግድያ በኋላ ድርጊቱ ብዙም ሲቀጥል የማናየው፣ሃጫሉ በተገደለበትም ወቅት  ጥቃቱ በተወሰነ አካባቢ ብቻ መጠንከሩ  የመንግስት መዋቅር እየፀዳ በመገኘቱና አክራሪዎቹ በመመንጠራቸውም እንደሆነም ይታመናል።
        የማህበረ ቅዱሳን መሪዎች ትናንት ያ ሁሉ መዓት ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ሲወርድ ምንም ያላላችሁት ፥ መቃወም ዋጋ ስለሚያስከፍል ሊሆን ይችላል።ለዕምነት ሲባል የሚመጣውን ሁሉ መቀበል የሚገባ ቢሆንም ፣አንዳንዴ ቅዝምዝሙን አጎንብሶ ማሳለፍ  እንደ ጥበብ የሚመለከቱት መኖራቸው እርግጥ ነው። ያን ሁሉ ጨለማ የታገሰ ቡድን  የዛሬው  ነፃነት ይበልጥ ምክንያታዊ  እንዲሆን ሊያደርገው በተገባ ነበር። ምክንያታዊነት ማለት ጥቃቱን ማን ለምን ዓላም ይፈፅመዋል የሚለውን መጠየቅ እና እንዴት ይቁም የሚለውን መመርመር ጭምር  ነው። 
      የማህበረ ቅዱሳን አባላትን “በንቃት ተከታተሉን” የሚል ጥሪ ማስተላለፍ ለተሸነፉ  እና ለሸሹ  እንዲሁም ለሃገራችን መዓት ለሚመኙ  ያስደስት ፣ያስጨበጭብ ይሆናል ። ከሌላው አማኝ  ጋር ተዋህዶ በዳር ሃገር ለሚኖረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኝ ግን የሞት ድግስ ጥሪ መሆኑን ክቃለምልልሱ ይበልጥ  መረዳት ይቻላል።አሻግሮ ማየት ለሚችል  በሃገር ላይ ቀውስ በበረታበት ግዜ እንደ ሕወሃት ያለ በግልፅ የቤተክርስቲያኒቱ ጠላት የሆነ መንግስት ቢሆን እንኳን ሕግና ሥርዓት እንዳይፍርስ መንግስት  መኖሩ የግድ ይላል።ሕግና ሥርዓት ሲፈርስ ዕልቂት ይነግሳልና!
            ግንቦት 11/2013      (May 19/2021)

Wednesday, October 21, 2020

“ኢሳይያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያ የሰጣት የመቶ ዓመት የቤት ሥራ” ሲሳይ አጌና

     

 
  " . . . ሻዕቢያ  ይበልጥ ያበሳጨን የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከመገንጠል የሚለውን አንኳር አቋማችንን አለመቀበሉ ነበር"  ገብሩ አሥራት  ገጽ 116 
 ". . .ሻዕቢያ እና ምዕራባውያን መቼም ቢሆን የኦነግን የመገንጠል  አጀንዳ ሲደግፉ አይቼ አላውቅም" ዶ/ር ነጋሶ ገጸ 152 
         . . .  More importantly, the very systems of government established in Ethiopia and Eritrea after the fall of the Derg were significantly different and not much appreciated in each other’s capital.  Isaias especially thought Meles’ concept of ethnic federalism was misguided. . . 
                                                                      David Shinn 
      የኤርትራው ፕሬዜዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ "ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥታናታል" ብለዋል  የሚለውን ከሩብ ክፍለዘመን በፊት ጀምሮ  አብዝተን ሰምተነዋል።በአንድ በኩል ይህን የሚገልጹልንን በማመን፥በሌላም በኩል በኢትዮጵያ የሆነውን እና የታየውን የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ በመመርመር በርግጥም ይህ የሻዕቢያ ዕኩይ ዕቅድ ሊሆን እንደሚችል ያመንን ጥቂቶች አልነበርንም።ይህ ሁኔታ  በአንድ በኩል ሕወሓትን ያለልክ ዝቅ አድርጎ ከመመልከት እና ሻዕቢያን ከማግዘፍም ይመነጫል።
         በእርግጥም ሕወሃት አዲስ አበባ ገብቶ ንግስናውን እስኪጭን “ወያኔ” እንደ  አማጺ ቡድን በሕዝብ ውስጥ ቢታወቅም፥መሪው አቶ መለስ ዜናዊ ግን አይታወቁም ነበር። አዲስ አበባ ገብተው የኢትዮጵያ ግዚያዊው መንግስት ፕሬዚዳንት  መሆናቸው ሲነገር በሕዝቡ ዘንድ ገጻቸውም፣ ስማቸውም  እንግዳ ነበር። በትግሉ ወቅት በመንግስት ሚዲያዎችም ስማቸው አይነሳም። በደርግ ዘመን ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚታውቁትን ያህል በኢትዮጵያ ሕዝብ  ውስጥ ሌላ  የሚታወቅ የዓመጽያን መሪም አልነበረም፣ ስለ ሰሜን ጦርነት፣ ስለ አማጽያኑ ሲወሳ  በስም የሚታወቁ እና የመንግስት ሚዲያም አርዕስት  የነበሩት ኢሳይያስ አፈወርቂ ብቻ ነበሩ።
      የሕወሃት/ኢሕአዴግ  ሃይል  መሃል ሃገር ገብቶ አምቦን ተሻግሮ ወደ አዲስ አበባ ሲገሠግሥ  የደርግ መንግስት አብዛኛውን እና ጠንካራ ሰራዊቱን ኤርትራ ለማቆየት መገደዱ በጦር ባለሙያዎች  ዓይን ምን ማለት እንደሆነ ባላውቅም ፥የደርግ መንግስት ለሕወሓት የነበረው ዝቅተኛ ግምት እስከመቃብርም  አለመለወጡን ከማሳየቱም  ባሻገር፣ይህ የደርግ መንግስት አስተሳሰብ በሕብረተሰቡም ዘንድ እንዲንጸባረቅ ምክንያት ሆኗል። ቤተ መንግስቱን ሊነጥቅ ያሰፈሰፈ ሃይል  እየገፋ መጥቶ ከመቶ ባነሰ ኪሎ ሜትር ተጠግቶ  ባለበት ሁኔታ አብዛኛውን ጠንካራ ሰራዊት ኤርትራ ማስቀመጥ ምን ማለት ነው?  ማዕከሉን ሰጥቶ ፣ቤተመንግስቱን ተነጥቆ የዳሩን መጠበቅስ ይቻላልን ? ጥያቄዬ  ለወቅቱ የሃገሪቱ መሪና  የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ነው። (ዕድሉን ባገኝ ለኮሎኔል መንግስቱ የማነሳቸው ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችም አሉኝ።ከፈቀዱ ዚምቧቤ ሄጄም ቃለምልልስ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ)
     ወደ ጉዳያችን  ወደ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ  እንመለስ።በአጠቃላይ ሕወሓት ከሻዕቢያ በኋላ መፈጠሩና  እስከ አዲስ አበባ በተደረገው ጉዞ የሻዕቢያ ድጋፍ እንዳልተለየው መነገሩም ፣ሕወሓትን ያለሻዕቢያ ድጋፍ ማሰብ ለብዙዎች አስቸጋሪ ሆነ። ሑለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ እና አስመራ ላይ  ስልጣን ከያዙም በኋላ በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ  የሻዕቢያ ተጽዕኖ እየጎላ መምጣቱ መሰማት ጀመረ፣ ቡና የማታመርተው ኤርትራ የኢትዮጵያን ቡና በብር እየገዛች ኤክስፖርተሮች ዝርዝር ውስጥ ገብታ ዶላር የማፈሷ ዜና ጎልቶ መወጣቱ ሕወሃት  ራሱን ችሎ የቆመ  መንግስት ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ  የሻዕቢያ ጉዳይ አስፈጻሚ ነው የሚለውም ገዢ ሃሳብ ወደ መሆን ተሸጋገረ።
      ኢትዮጵያ ውስጥ ሻዕቢያ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ  ስላላጠራጠረም  ሃገራችን የገባው  የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ የሻዕቢያ አጀንዳ መሆኑም ጥቂት በማይባሉ ወገኖች ዘንድ  ታመነ ። ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ “ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ  ሰጥተናታል” ያሉትም ይህንን የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ መሆኑም ይተነተን ጀመር።
 በኋላ ላይ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መጀመሩ ተረት እና ዕውነቱን ለማበጠር ፣ ስለ ሁለቱ ሃይሎች ይበልጥ ለመርመር አይን ገላጭ ክስተት ሆነ።
        ሻዕቢያ እና ሕወሓት በግንቦት ወር 1990 ጦርነት ውሳጥ ሲገቡ፣ ደም እየፈሰሰም  ጦርነቱ የምር መሆኑ ብዙዎችን አጠራጠረ።ነፍሳቸው ይማረውና  የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው  መመህር ዶ/ር መኮንን ቢሻው  የመቀሌው አይደር ት/ቤት በቦምብ እስኪደበደብ  ጦርነቱ የዕውነት አልመሰለኝም ሲሉ በወቅቱ  ለ”ኢትኦጵ” ጋዜጣ የገለጹት የጥርጣሬው ስሜት የተራው ሕዝብ ብቻ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው። ሕወሃትን ያለሻዕቢያ  ማሰብ ምን ያህል ከባድ እንደነበርም  የሚያስረዳን  ዶ/ር መኮንን ቢሻው በዚያው ቃለ ምልልስ   “ያም ቢሆን  መጣላታቸውን መቶ በመቶ አላመንኩም ፣ገና 60 በመቶ ላይ ነኝ “  ማለታቸው ስናስታውስ ነው።
    ሕወሃትና ሻዕቢያን ለያይቶ መመልከት በወቅቱ ምን ያህል ከባድ እንደነበር ወቅቱን  እና ግኑኝነታቸውን ለሚያስታውስ ግልጽ ነበር። በነገራችን ላይ ዛሬም ድረስ አልተጣሉም ብለው የሚያምኑ  “የፖለቲካ ሊቆች”  መኖራቸውን  በዚሁ አጋጣሚ ማስታወሱና እግዚአብሄር እንዲምራቸው መመኘቱም ተገቢ ነው።
       ጦርነቱ ሲቀጥል ፣ እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ ችግሩ እንዴት ጀመረ  የሚለውን መመርመር እና መጠየቅ  ማንበብ እና መረጃ መቆፈር የግድ ይላል።   ለምን ተጣሉ? የቀደመ ግኑኝነታቸውስ  ምን ነበር የሚለውን ስመረምር ግን የኢሳይያስ “የመቶ አመት የቤት ሥራ “ የሕወሃት ሆኖ ጠበቀኝ።ሻዕቢያና አቶ ኢሳይያስ ከሕወሃት ጋር ግጭት ውስጥ የገቡበት የጸቡ አንዱ ሰበዝ  እኛ የምንታመምበትን የዘር ፖለቲካ ሻዕቢያ በመቃወሙ እንደሆነ አሜሪካዊው  ዲፕሎማት ኽርማን ኮኽን  ጽፈው ሲያስነብቡን ፥ ሻዕቢያ የትግራይ እና የኦሮሞን   መገንጠል በአጠቃላይ የኢትዮጵያን መበታተን  አይደግፍም ብለው የኦነጉ አቶ ሌንጮ ለታ  እና  የሕወሃቱ አቶ ገብሩ አስራት  እንዲሁም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና  አቶ መለስ ዜናዊ ሲመሰክሩና በዚህም ከሻዕቢያ  ጋር መቀያየማቸውን በኩራት ሲነግሩን  ሻዕቢያ በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን  የክፉ ቀን ከለላ ስለሆነን ብቻ  ሳይሆን፣ በዘላቂነትም ወዳጃችን መሆኑ ይገለጥልናል።27 ዓመታት ያሳመሙን ፣ዛሬም ከሸሹ በኋላ በዘሩት በሽታ የሚያሰቃዩን የሕወሃት መሪዎች መሆናቸውም ይከሰትልናል። የሁሉም ምስክርነት በጽሁፍ፣በመጽሃፍ እና በቪዲዮ የተደገፈ በመሆኑ በዝርዝር እንመለከተዋለን። ጦርነቱ ሲጀመር የነበረውን  ሁኔታ ግን በቅድሚያ እናስታውስ ።
        የዛሬ 22 ዓመት ከ 5 ወር  ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ በኢትዮጵያ ፓርላማ ቀርበው የመስሪያ ቤታቸውን የአንድ ዓመት  አፈጻጸም ሪፖርት አቀረቡ።በዚህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ያላት ግኑኙነት ሰላማዊ መሆኑንም ገለጹ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የአቶ ተፈራን መግለጫ በምስል አስደግፎ ዕለቱኑ ዘገበ።
    በማግስቱ  ግንቦት ቀን  5/1990  ዓ/ም ፍጹም ያልተጠበቀ ፥የአቶ ተፈራ ዋልዋን  መግለጫ የሻረ እና ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መፈጸሟን  የሚገልጽ ያልተጠበቀ ዜና በዚያው  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ተላለፈ።   
    አቶ ተፈራ ዋልዋ ዙሪያው ሰላም ነው የሚል  መግለጫ  በሰጡ ማግስት የመጣው ይህ ዜና ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንግዳ ቢሆንም፥ መንግስታዊዎቹ ሚዲያዎች የመንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሰው እንደዘገቡት ትንኮሳው የታየው እና በታንክ የተደገፈው ጥቃት የጀመረው ከሳምንት በፊት ሚያዚያ 28/1990 ነበር።
    ያው እንግዲህ አቶ ተፈራ ዋልዋ መከላከያ ሚኒስትር ቢሆኑም ብአዴን እንጂ ህውሃት ባለመሆናቸው፣ የሆነውንም እየሆነ ያለውንም የሰሙት ያው ከኛው ጋር ነበር ማለት ነው። 
   የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም  ጦርነቱ እስከተከሰተበት ግዜ ድረስ  በኢትዮ ኤርትራ ግኑኝነት  ዙሪያ ተሳታፊ  እንዳልነበሩ "ዳንዲ-የነጋሶ መንገድ" በተባለው መጽሃፋቸው ገጽ 174  ላይ  አስፍረዋል። "እስከ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት  በኤርትራ ጉዳይ ላይ ሲካሄዱ በነበሩት ውይይቶች ላይ አልተሳተፍኩም" ብለዋል።
   ዶ/ር ነጋሶ በዚህም ቅር ይላቸው እንደነበር በዚሁ መጽሃፋቸው ገጽ 222 ላይ አስፍረዋል።ከኤርትራ ጋር  ግኑኝነት እንዲያደርግ በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ሁሉም የሕወሃት አባላት እንደነበሩ ያስታወሱት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ  የፈጠረባቸውን ስሜት ሲገልጹም
" ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ቅሬታ ነበረኝ። እኛን ደብቀው ውስጥ ውስጡን ሲሰሩ ቆይተው አሁን የሚነግሩን እንዴት ነው የሚል ቅሬታም  በውስጤ ተፈጥሮ ነበር" ብለዋል።
    እርግጥ ነው በኢትዮ ኤርትራ ግኑኝነት ዙሪያ ኢትዮጵያን ወክለው ሲሳተፉ የነበሩት ሁሉም የሕወሓት አባላት እንደነበሩ የሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት  አቶ ገብሩ አስራትም ግልጽ አድርገዋል።አቶ ገብሩ አሥራት "ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ" በተባለው በ2006 በታተመው  መጽሃፋቸው በገጽ 268 እንዳሰፈሩት ጦርነቱ እስኪፈነዳ  ኢትዮጵያን ወክለው  ከኤርትራ ልኡካን ጋር  ይነጋገሩ የነበሩት  ሶስቱ የህወሃት  ሰዎች  ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ፣ አቶ ተወልደ ወልደማርያም እና አቶ ክንፈ ገብረመድህን ነበሩ።
           ሕወሃት እና ሻዕቢያ በግንቦት ወር 1990 የጀመሩት እና ሁለት ዓመታት    የዘለቀው  ጦርነት በይፋ የሚታወቀው ምክንያቱ የባድመ ይገባኛል ቢሆንም፣ የተጠራቀሙ ችግሮች  እንዲሁም  በኢትዮጵያ የተዘረጋው የጎሳ ፌደራሊዝም  የልዩነት ነጥብ ሆኖ መገኘቱን  ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን ይገልጻሉ።በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን የዛሬ 7 ዓመት January 2014  ጽፈው እንዳስነበቡን  በኢትዮጵያ የተዘረጋው የጎሳ ወይንም የብሄር ፌደራሊዝም  በኤርትራውያን በተለይም በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል፣የተሳሳተ መንገድ ስለመሆኑም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
Time to Bring Eritrea in from the Cold (But It’s Harder than It Sounds) – By David Shinn
. . . While the Tigrayan People’s Liberation Front (TPLF) of Meles Zenawi and the Eritrean People’s Liberation Front (EPLF) of Isaias Afewerki often cooperated in their battle to remove the Derg regime from Ethiopia, they also periodically had tactical and strategic differences.  In the post-Derg euphoria, these earlier disagreements were usually overlooked by outsiders.  More importantly, the very systems of government established in Ethiopia and Eritrea after the fall of the Derg were significantly different and not much appreciated in each other’s capital.  Isaias especially thought Meles’ concept of ethnic federalism was misguided. . . 
              (አርቲክሉን ሙሉን በዚህ ሊንክ ያገኛሉ)
 https://africanarguments.org/2014/01/13/time-to-bring-eritrea-in-from-the-cold-but-its-harder-than-it-sounds-by-david-shinn/
     ይህንን የዲፕሎማቱን ትንተና የሕወሃት ፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት "ሉዓላዊነት እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵይ" በተባለው እና በ2006 በታተመው መጽሃፋቸው ገጽ 236 ላይ  ይህንኑ በማጠናከር  የሁለቱ ቡድኖች ልዩነት ወይንም ቅራኔ ከወሰን ይገባኛል የተለየ  እንደሆንም በሚከተለው መልክ ይገልጹታል። 
    " ሻዕቢያዎች ከሕወሀት/ኢሕአዴግ ጋር የተወሰኑ የፖለቲካ ልዩነት እንዳላቸው፥ ከስትራቴጂ አንጻር ግን ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌላቸው ይገልጹልን ነበር።ልዩነት የሚሏቸውንም በሥጋት ደረጃ ብቻ  የሚያነሷቸውን ኢሕአዴግ የሚያራምደውን የብሄር ብሄረሰብ መብት  እስከመገንጠል  አቋምና ይህንን መሰረት ያደረገውን  አወቃቀር ነበር።ይህ በኢትዮጵያ የተቋቋመው የፌደራል ሥርዓት ለግጭት እና  ለኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል  ሊዳርግ  ይችላል የሚል ሥጋት እንደነበራቸውም በግልጽ ይነግሩን ነበር።ከዚያ ውጭ ሌላ የፖለቲካ ልዩነት እንደሌላቸው እና ከኛ ጋር የሚኖራቸው ግኑኝነትም ስትራቴጂካዊ ሊሆን እንደሚችል ይገልጹልን ነበር”
         አቶ ገብሩ አሥራት ይህንን በመጽሃፋቸው ገጽ 116 ላይ ሲያጠናክሩም
  " ሻዕቢያ  ይበልጥ ያበሳጨን የብሄር ብሄረሰብ መብት እስከመገንጠል የሚለውን አንኳር አቋማችንን አለመቀበሉ ነበር" 
      አቶ ገብሩ በመጽሃፋቸው እንዳሰፈሩት ሻዕቢያዎች የልዩነት ነጥብ  በማለት የሚያነሱት እና እንደ ሥጋት የሚጠቅሱት የኢሕአዴግን የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት እስከመገንጠል  የሚለውን እና  ይህንን መሰረት ያደረገውን የፌደራል ሥርዓት አወቃቀር ነበር።ሻዕቢያዎች ይህ ሁኔታ  ለግጭት እና ለኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል  ይዳርጋል የሚል ሥጋታቸውን ይገልጹ  እንደነበርም የሕወሃቱ አቶ ገብሩ  አሥራት በመጽሃፋቸው ያስታውሳሉ። ይህንን የሻዕቢያ አቋም ሕወሃት መጨረሻ ላይ ከደረሰብት ውድቀት እና ሃገሪቱ ላይ ጥሎ ካለፈው መከራ አንጻር በመመዘን በእርግጥም የኢትዮጵያ ጠላት ማነው የሚለውን ጥያቄም አድምቆ ማስመር ያስፈልጋል።
     ሟቹ  የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት የቀድሞው የኦነግ አባል  ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም  በኦነግ እና በሻዕቢያዎች መካከል ስለነበረው ግኑኝነት ሲጠቅሱም  ሻዕቢያ  ኦነግን የሚረዳው ደርግን ለመጣል እንዲያግዘው ነው ይላሉ። ሻዕቢያ የኦነግን የቅኝ ግዛት ጥያቄ እንደማይቀበል እና  በኦሮሚያ ያለው የፊውዳል መስፋፋት እንጂ ቅኝ ግዛት አይደለም እንደሚል  የዳንዲ መንገድ በተባለው መጽሃፋቸው ገጽ 115 ላይ አስፍረዋል።ዶ /ር ነጋሶ ይህንኑ  በገጽ  152 ላይ ሲያጠናክሩም፦"ሻዕቢያ እና ምዕራባውያን መቼም ቢሆን የኦነግን የመገንጠል  አጀንዳ ሲደግፉ አይቼ አላውቅም" ብለዋል።  ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ መጽሃፋቸው በገጽ  172 ላይ ደግሞ
"ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ ተጽዕኖ የማሳረፍ ውጥኑን ለማሳካት ሲል ሕወሃትም ሆነ የኦሮሞ ድርጅቶች ተባብረው ደርግን እንዲጥሉ ቢፈልግም የእሱ ዓይነት የነጻነት ጥያቄ  እንንዲያነሱ ግን አይሻም ነበር” 
       ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም  የኤርትራ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት በተባለውና  በአቶ አብርሃም ያየህ ከትግርኛ ወደ አማርኛ በተመለሰው  መጽሃፍቸው  ገጽ 170  "የራስን ዕድል በራስ መወሰን ጥያቄ ላይ የተነሳ ልዩነት" በሚል ንዑስ ርዕስ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ የብሄረሰቦች የመገንጠል መብትን በመቃወም ሕወሃት ለሃገራዊ አንድነት እንዲታገል ያቀረበውን ጥያቄ አንስተው ይተቻሉ።በዚህም ግኑኝነታቸው መሻከሩን በኋላም  መቋረጡን ያብራራሉ።
          የኦነግ መስራች እና ጸሃፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታም በኢሳት ቴሌቪዥን     March 2016 ባደረጉት ቃለምልልስ  ሻዕቢያ የሕወሃትንም ሆነ የኦነግን የመገንጠል ጥያቄ እንደማይቀበል ይልቁንም ለአንዲት ኢትዮጵያ እንዲሰሩ ግፊት ያደርግ እንደነበር በድምጽ እና በምስል መስክረዋል። (ከተያያዘው ቪዲዮ ከ15 ኛው ደቂቃ ጀምሮ የአቶ ሌንጮን   ምስክርነት ይስሙ)
     https://www.youtube.com/watch?v=cYRNyDCJjiU
       ሌሎች የጽሁፍ እና የድምጽ ምስክርነቶችም ከላይ የተዘረዘረውን የሚያጠናክሩ ሆነው አግኝቺያለሁ።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በNovember 2015 ከኢሳት ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ፣ዶ/ር ካሳ ከበደ October 2015 ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በተካሄደው የኢትዮ ኤርትራ ኮንፈረንስ ላይ ያደረጉት ንግግር ወዘተ ተረቱን የሚደፍቁ ፣የነ አቶ ገብሩ አስራትን ምስክርነት የሚያረጋግጡ ናቸው። በአጠቀላይ የኢሳይያስ አፈወርቂን “ጸረ ኢትዮጵያ አጀንዳ”  እና “የመቶ ዓመት የቤት ሥራ” ስፈልግ ያገኘሁት  ዕውነታ  ይህ ነው።
       ይህም ብቻ አይደለም።ሰለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ብሄራቸው መብት የተከራከሩና ፍትህ የጠየቁ  በወህኒ በሚሰቃዩበት፣የሸሹም ከጎረቤት ሃገራት ጭምር በሚታፈኑበት ፣ ሕወሃት ምድሩንም ሰማዩንም በተቆጣጠረበት በዚያ ጨለማ ዘመን ብቸኛ መሸሻ ፣ለመታገልም መንደርደሪያ እና መጠጊያም የነበረችው በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የምትመራው ኤርትራ ነበረች፣ከለውጡም በኋላም ሕወሃቶች  የነርሱ ጸጥታ መዋቅሩ ከመጽዳቱ በፊት  ያበጠው ይፈንዳ ብለው የግልበጣ ሙከራ ያላደርጉት ቀውሱ አሳስቧቸው ወይንም የምዕራባውያኑ ተግሳጽ አስጨንቋቸው ብቻ ሳይሆን፣የኤርትራን መንግሥት  በመፍራት ጭምር መሆኑንም መጠራጠር ይቻላል። 
     ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ቡድናቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሊወዳጁ እንደሚችሉ የሕወሃት መሪዎች አስቀድመው ቢገምቱ ኖሮ መጋቢት 24/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዓለ ሲመት መሆኑ ቀርቶ፣ሁለት ዓመታት የቀጠለው ቀውስ ወደ ከፋ ዕልቂት የሚያመራበት ምዕራፍ መጀመሪያም ይሆን ነበር። ሓምሌ 1 ቀን 2010  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ አስመራ፣ሃምሌ 7 /2010 ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ የሕወሃት መሪዎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ እና አርፈው እንዲቀመጡ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል ተብሎም ይታመናል።የለውጡን ሃይል  በቀጥታ ከመታገል ይልቅ በየክልሉ ቀውስ ስፖንሰር ማድረግ የመረጡት ፊትለፊት ከግንብ ጋር መላተሙ ስለማያዋጣ እና ተራራውን መግፋት እንደማይቻል በማመናቸው ጭምር ነው።  . . . አዎን ትርክቶችን  አምነን ፣ መጽሃፉን ስንገልጥ ያገኘነው ዕውነትና ዛሬ ያለንበት ሁኔታ  ይህ ነው።የቀረው ተረት ነው።    
        ፕሬዚዳንት ኢሳይያስም ሆኑ፣ የኤርትራ መንግስት  ትናንትም ሆነ ዛሬ  የኢትዮጵያ ጠላት አለመሆናቸውን እንዳረጋገጥን ሁሉ ነገም ጥሩ ወዳጀ እና ወንድም ሆነው እንደሚቀጥሉ እናምናለን።ከኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ ለትውልድ የሚቀርበው ትልቁ ገጸ በረከት የትናንትን ፋይል ዘግቶ፣ ለነገ የተደላደለ ጥርጊያ መዘርጋት ነው።
            ጥቅምት 5/2013  October 15/2020

 https://youtu.be/j1e9coCeP5g
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

Monday, June 3, 2019

በመንገጫገጭም ውስጥ የሚታይ ደማቅ ለውጥ አለ!! ሲሳይ አጌና


       በኢትዮጵያ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ለውጥ በብዙ ፍላጎቶች እንዲሁም ሥልጣናቸውን በተነጠቁ ወገኖች  እና  የፖለቲካ ንግድ ላይ በቆዩ ሃይሎች ፈተና እየገጠመው  መሆኑ ግልጽ ነው።ይህ ዛሬ የሚታየው መንገጫገጭ  ግን የትናንቱን የመቃብር ሕይወትና የመቃብሩን ጥልቀት በፍጹም ሊያስረሳን አይገባም።

         ኢትዮጵያውያን ያለፍንበትን መከራ በማሰላሰል ብቻ ሳይሆን መውጫችን ምንድነው ብለን የተጨነቅንበትን ግዜ መልሰን ስንቃኝ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ በጉንፋን የሚመሰል ቀላል ሕመም ሲሆን፥በየአካባቢው ያለው ቆሻሻ ድርጊት ከቀጠለ እና የዕልህ  ጉዞው " በእኛ እና እነሱ" ቅኝት ከዘለቀ ግን  ጉንፋኑ  ተስቦ ሆኖ ሁላችንንም እንደሚያጠፋ ከጥርጣሬ ባሻገር መናገር ይቻላል።መንግስት የየአካባቢው ጉልበተኞችን እንዲያስታግስ ፥ ሕዝቡም ራሱን ከጎበዝ አለቆች   ስብከት  እንዲጠብቅ  መወተወቱ እጅግ አስፈላጊ  ነው።ጨለማ መልሶ እንዳይወርሰን  ከጨላማ ሰባኪዎች ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል። ትናንት የነበርንበትን ጨለማ ብቻ ሳይሆን፥ ከጨለማ ለመውጣት የነበረው መንገድ ሁሉ በራሱ ጽልመት የወረሰው መሆኑን በማስታወስ ዛሬን በከፍተኛ ሃላፊነት እና ጥንቃቄ  እንድንጓዝ  ግድ ይለናል።

    በዛሬው  (መጋቢት 30/2011)  "ለውጥማ አለ!?" በሚል ርዕስ በዚህ በብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ  "ብራና" ባዘጋጀው መድረክ  አርዕስቱን መሰረት አድርገው የሚነሱ ጥያቄዎችን በተለይም ለውጥ የለም በሚል የሚሰሙ ድምጾችን በቀጣዮች  ነጥቦች  እናስልለውና (እናድክመውና)  የለውጡን ትርጉም ከለውጡ ዋዜማ ሁኔታ አንጻር እንፈትሸው።

   

  

   አሸባሪ የተባለው ሚዲያ "ኢሳት"  ጋዜጠኛ  በአዲስ አበባ ብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ ከናንተ ጋር እየታደመ ፥የሃገሪቱ ወህኒ ቤቶች ከፖለቲካ እስረኞች በጸዱበት፥ ጠመንጃ ያነሱትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሃገራቸው  በተመለሱበት ፣ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ለሁለት የተከፈለቸው የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  አንድነቷ በተረጋገጠበትና መንበራቸውን በፖለቲከኞች ውሳኔ የተነጠቁት ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ ሥፍራቸው  በተመለሱበት፥የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ወህኒ የተቆለፈባቸው  የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ስለዕምነታቸው በነጻነት በመስጊዳቸው  በሚወያዩበት ፣ እንደ ርሥት 27 ዓመታት በሙሉ  በአንድ ሰፈር ሰዎች በባሌበትነት የተያዙ የሥልጣን ቦታዎችን ሌሎችም ሲከፋፈል እያየን፣ አሳሪዎች በወንጀል ተጠርጥረው  እነርሱም በተራቸው  ውህኒ ገብተው  አቤቱታ ሲቀርቡ እየሰማን ወዘተ ለውጥ የታለ ብሎ የሚጠይቀውን ፥በግሌ  ለውጥ ምንድን ነው  ማለቱን መርጬያለሁ።

 ይህ ለውጥ ካልሆነ ምን ብለን እንጥራው  ይሆን ስያሜ ይስጡን እና እንሟገትበት።

    በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ  ትርጉም የሚኖረው መቃብር ውስጥ ለነበረው ሁሉ ቢሆንም  ፥የመቃብሩን ጥልቀት ይበልጥ የሚረዳው ግን ከመቃብሩ ውስጥ ለመውጣት የተፍጨረጨረውና መውጫውን ያሰላሰለው ብቻ ነው።

ይህንን ከላይ  እንደጠቀስኩት የራሴን አጋጣሚ በማንሳት ላብራራው።

  በምኖርበት አሜሪካ  ቨርጂኒያ ግዛት  "ሊዝበርግ ፓይክ "በተባለ  መንገድ ላይ የሚገኝ "ስታር ባክስ" የሚሉት ቡና መሸጫ አለ።ይሄ ቤት በብዛት የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ  ዜጎች ይሰባሰቡበታል።ምናልባትም ሞቃዲሾ ያላችሁ ያህል እንዳይሰማችሁ የሚያደርገው ሞቃዲሾን አለማውቃችሁ ወይንም ጥቂት ነጮች እንዲሁም ስፓኒሾች እና  የኤዢያ ሰዎች በማየታችሁ  ሊሆን ይችላል።

    ታዲያ እዚህ ቡና መጠጫ ሱቅ ውስጥ  ሁልግዜ ሶማሊያውያን ተሰብስበው  ሳይ ሃገር አልባነታቸው ይመጣብኛል። በሕይወቴ ተስፈኛ የሆንኩትን ሰው ተስፋ ቢስ ያደርጉኝ  እና ኢትዮጵያን መልሼ ማግኘቴ ወይንም ማየቴ  ከነአካቴውም ኢትዮጵያ  በሕልወናዋ መቀጠሏ  ያጠራጥረኛል።እናም ከዚህ ቡና መሸጫ ትኩሱን ቡና ይዤ ስወጣ በበጋ ሙቀት ብርድ ብርድ እያለኝ ፥ፊቴ ጭጋግ ለብሶ   መፍትሄው ምን ይሆን ?እያልኩ ይበልጥ አሰላስላለሁ። 

   ሥልጣን ላይ የነበረው ቡድን እና መንግስት እንደሚወድቁ  ጨርሶ ተጠራጥሬ  ባላውቅም  የሚተካቸው ማነው? ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ጥላቻ በተሰበከበት እና ተረት ታሪክን በተጫነበት  ሃገር ፥ልዩነት ጌጥ እና ውበት መሆኑ ቀርቶ የጥላቻ እና የግጭት  መንስኤ እንዲሆን  መንግስታዊ እና የፓርቲ መዋቅር  በሚተጋበት ሃገር   አፋኙ እና ዘረኛው ሥርዓት ሲወገድ  የሚተካው ማነው ? እንዴትስ  ይወገዳል ? የሚለውን ብርቱ ጥያቄ  እያሰላሰልኩ በዚሁ በቨርጂኒያ "ሊዝበርግ ፓይክ"  ጎዳና  ተመላልሺያለሁ። 

          ብዙ ሳስብ ፥የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ሥመረምር  ከብርሃን ይልቅ ጭለማው እየበረታብኝ ፣ያለንበት የመቃብር ጥልቀትም ይበልጥ   እየተገለጸልኝ  መጣ ።  ከሃገሬ የራቅኩት 12 ሺህ ያህል ኪሎሜትር ቢሆንም  ውስጤ የገባው ሥጋት   ኢትዮጵያን ጨርሶ የማልደርስባት አደረገኝ።  ከማርስ በላይ በአያሌ ሚሊዮኖች ኪሎሜትር   ኢትዮጵያ ራቀችብኝ። እንዴት ልድረስባት? ማን እንዴት ከዚህ መከራ ይገላግለን? መፍትሄ ፍለጋ አማተርኩኝ።አማራጭ ማሰስ ጅርመርኩኝ።

  1ኛ/ከኤርትራ የሚነሱ አማጽያን  ከዚህ መከራ ይገላግሉን ይሆን? በሚል እነርሱ ላይ በማተኮር  አቅማቸውን፥ትብብራቸውን እና የኤርትራን መንግስት ድጋፍ  ለመመርመር ሞከርኩኝ።እነዚህ ብረት ያነሱና  የኤርትራን መንግስት ከለላ ያገኙ  አማጽያ  አርበኞች ግንቦት 7፣ኦነግ፣አዲሃን፣ትህዴን፥ ARDUF፣ONLF ወዘተ  በጋራ  ቢሰሩና የትብብር ግንባር  ቢፈጥሩ ሥርዓቱን በሃይል አሰውግደው ሥልጣን መያዝ ይችላሉ ወይ ለሚለው  ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ሥርዓቱን ለመጣል የሚያስችላቸው ቢሆንም ፥ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ እና መረጋጋት የሚወስድ  መሆኑ ግን አጠራጣሪ ብቻ ሳይሆን አስፈሪም ነበር።

    

  ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ በመዳከሙ እንዲሁም በሙሉ ልብ እና በግልጽ አማጽያኑን የሚረዳ የጎረቤት ሃገር መንግስት መኖሩ  ብረት ያነሱት የኢትዮጵያ ሃይሎች  በቀላሉ እና በፍጥነት የማሽነፍ  ዕድል እንደሚኖራቸው  በኡጋንዳ ሚልተን አቦቴ  በኋላም ይዌሪ ሙሰቬኒ እንዲሁም በኮንጎ ሎራን ካቢላ በታንዛንያ እና በርዋንዳ መንግስታት ድጋፍ በወራት እንቅስቃሴ  ኢንቴቤ እና ኪንሻሳን  መቆጣጠራቸውን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል።

        ችግሩ ብረት ያነሱት የኢትዮጵያ ሃይሎች  የተበታተኑ እና ተባብረው ለመስራት  አለመፈለጋቸው ነው፥በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ኢትዮጵያ ከሚሉ ሃይሎች ጋር ለመንቀሳቀስ   አለመፍቀዱ በኢትዮጵያ በወታደራዊ ሃይል መንግስት በመቀየር የተረጋጋ ሃገር  ለመፍጠር እና ዲሞክራሲያዊ   ሥርዓት ለመመሥረት ያለውን ዕድል ብርቱ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶት ቆይቷል።ቡድኖቹ ተነጣጥለው ቢሄዱ እና ተሳክቶላቸው ቢያሸንፉ እንኳን ኦነግ ከኦሮሚያ ክልል ውጭ ተቀባይነት አይኖረውም።በሌላም በኩል አርበኞች ግንቦት 7 ቢያሸንፍ  ሀገሪቱን በበከላት የዘር ፖለቲካ ሳቢያ ይህ ቡድን ቢያንስ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል ተቀባይነት ማግኘቱ በእጅጉ አጠራጣሪ ነው።እንደተበታተኑ በየሰፈራቸው ቢያሽንፉ ድግሞ ሃገሪቱ ባልተቁረጠ የዕርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መዘፈቋ የማይቀር ይሆናል።

    ሥለሆነም በወታደራዊ ሃይል የነበረውን ሥርዓት ማፍረስ ቢቻልም፥የተርጋጋ ሃገር እና መንግስት ማምጣት እንደማይቻል ሲታየኝ  ከመከራ የምንፈታበት፥ መዳኛችን ምን ይሆን በሚል ሌላ መውጫ አሰላስላለሁ። 

2/ሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማስወገድ ያለው ሌላው  አማራጭ ሕዝባዊ ዓመጽ  ወይንም  ሕዝባዊ ዕምቢተኝነት ነው።ሕዝባዊ ዓመጽ ደግሞ በመጨረሻው ምዕራፍ መልክ የሚይዘውና ፍጻሜ የሚያገኘው በወታደሩ ጣልቃገብነት  እና ግፊት መሆኑም ይታወቃል።በኢትዮጵያ ያለው ወይንም  የነበረው የሰራዊቱ አደረጃጀት እና አመራሩ ሲታይ በሕወሃት ፍላጎት የተዋቀረ እና በሕወሓት ታጋዮች ቁጥጥር ሥር የሚገኝ በመሆኑ  የሕወሓትን አገዛዝ ለማስወገድ የሚደረግን ትግል እንኳን ደግፈው ሊቆሙ ገለልተኛ ሆነው እንኳን እንድማይታዘቡ ይልቁንም ወደ ጭፍጨፋ ሊያመሩ እንደሚችሉም ሳይታለም የተፈታ ነው፥በተግባርም ያየነው ይህንኑ ነው።

     ከ15 ዓመታት በፊት  በዩክሬን ኬቭ እና በጆርጂያ  ቲቢሊሲ ጎዳናዎች የታየው ኦሬንጅ እና ሮዝ  ሪቮሉሽን(የብርቱካን እና ጽጌረዳ አብዮት) እንዲሁም በቅርብ ዓመታት እ/ኤ/አ  በታህሳስ  2010 በቱኒዚያ የተነሳው  እና  በአረቡ ዓለም በተቀጣጠለው  የሞሃመድ ቡዓዚዝ አብዮት ዙፋናቸው ላይ ሲንገታገቱ የነበሩት አምባገነኖች ወንበራቸውን የተነጠቁት በወታደሩ ጣልቃገብነት  አሊያም  ዓመጹ ባስከተለው የትጥቅ ትግል መሆኑ ይታወቃል።

    ሕዝባዊ ዓመጹ ወደ ትጥቅ ትግል ያመራባቸው ሊቢያ እና የመንን የመሳሰሉ ሃገራት ደግሞ አምባገነኖቹን ኮሎኔል  ሙዓመር ጋዳፊን እና አሊ አብደላህ ሳላን ቢገላገሉም  ሃገራቱ  አሁንም በቀውስ ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።ሕዝባዊ ዓመጹ ብቻውን መፍትሄ  ያስገኘባቸውን ሃገራት ግብጽን እንድምሳሌ ብንወስድ እንኳን ሕዝባዊ ተቃውሞው የተገታው እና የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ስንብት የተከተለው  በወታደሩ እና በጸጥታ ሃይሉ ጣልቃገብነት ነው።

   ከላይ እንደተመለከትነው በኢትዮጵያ የነበረውን የወታደሩን አወቃቀር  ስንመረምር  በሕዝባዊ ዓመጽ ለለውጥ የሚነሳውን ሃይል ወታደሩ የሚደግፍ ሳይሆን ፥የሚጨፈልቅ በመሆኑ  በሕዝባዊ ዓመጽ በኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣትን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ታዲያ እንዴት ለውጥ ሊመጣ ይችላል? ስል ቆይቺያለሁ።በወታደራዉ መፈንቅለ መንግስት ለውጥ እንዳይመጣ  አመራሩ በሕወሓት ሰዎች በመያዙ ከላይ ግልበጣ ማድረግ  የማይታሰበውን ያህል፥ከሥር የሚነሱ ዝቅተኛ መኮንኖችም በዘር በተከፋፈለ ሰራዊት ውስጥ ወታደራዊ ግልበጣ የማድረግ ዕድላቸው ዜሮ ነው ማለት ይቻላል።ቢሳካለቸው እንኳን ሰራዊቱ በዘር ተከፋፍሎ ይታኮሳል እንጂ  ሕወሓትን ከቤተ መንግስት ማውጣት አይቻለውም። 

      ታዲያ  ሃገሪቱ ወደ ቀውስ ከምታመራ ዘረኝነት እና ዘረፋን የአመራር ፍልስፍናቸው  ያደርጉት ሕወሓቶች የጫኑብንን  ባርነትን ፈቅደን፣ዘረፋውንም  ይሁንላቸው  ብለን  ብንተዋቸውስ  እንኳን  ሃገሪቱን ብድር ማጥ ውስጥ ከተው የሃገሪቱን  ኢኮኖሚ ፈተና ላይ የጣሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ በመውደቃችን ፥እነሱም በሥልጣን ኢትዮጵያም በሕልውናዋ መቀጠሏ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

  

         እንዲህ ግራ ተጋብቼ ፥ዕይዝ እጭብጠው ቸግሮኝ  ባለሁብት እና  እንደጎረቤት ሶማሊያ ዜጎች  ሃገር አልባነት  እየተሰማኝ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ዓመጽ ተስፋ ቢዘራብኝም  መድረሻው የት ይሆን  የሚል ብርቱ ስጋትም አልተለትልየኝም ነበር።

      የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዓመጽ ከግብጽ እና ቱኒዚያ የተለየ፣ ከሊቢያ እና የመን የባሰ አደጋ የሚደቅን በይበልጥም ወደ ሶርያ የተጠጋ መሆኑ ይታየኝ ነበር።በሶርያ በአንድ ዕምነት ተከታዮች ማለትም "የሺአ" ሙስሊሞች ውስጥ "አለዊት" የሚባለው ሴክት ወይንም ክፍል የሃገሪቱን መሪነት፣ ጸጥታ እና መከላከያ  በመቆጣጠሩ ሕዝባዊውን ዓመጽ በጉልበት ለመጨፍለቅ ተንቀሳቀሰ ፥በውጤቱም ለአሸባሪዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ።በዚህም ዛሬ ሶሪያ በተለይም ጥንታዊቷ ከተማ  አሌፖ ፈራርሳ   ነዋሪዋቿም  የምድር ሲኦል ውስጥ ወድቀዋል።  

  ግጭቱ ከተፈጠረበት ኤ/አ/አ 2011 እስከ ሜይ 2013  በሁለት ዓመት ብቻ 94 ሺህ  ሰዎች መሞታቸውን  Syrian Observatory for human rights የተባለ መቀመጫውን ብሪታንያ ያደርገ 

 ተቋም  ገልጿል።ባለፉት 8 ዓመታት  የሟቾቹ ቁጥር 400 ሺህ መድረሱን በሶርያ የተባበሩት መንግስታት እና የአረብ ሊግ መልዕክተኛ ይፋ አድርገዋል።

      

     በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሃገሪቱን አንድነት የጠበቀና ዕልቂትን የቀነሰ ለውጥ እንዴት ይመጣል ብለን  ግራ በተጋባንበት አንዲት ጥይት ሳይጮህ  በኢትዮጵያ  የተከሰተውን ለውጥ  ተዓምር ብለን እንዳንጠራው ዛሬ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ አሳዛኝ ክስተቶች  የሚያግዱት አይሆንም።ያን  አስፈሪ የተባለውን ሁኔታ በእግዚ አብሄር  ርዳታ እና በለውጥ ሃይሉ ጥረት የተሻገርን ቢሆንም ዛሬም ኢትዮጵያን ወደ መከራ ሕዝቧንም ወደ ዕልቂት ለመክተት የሚረባረቡ ሃይሎች መኖራቸውን እያየን  በመሆኑ ሁላችንም ዕረፉ ልንላቸው ይገባል።ሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖችም የችግሩን አሳሳቢነት እና የአደጋውን ሥፋት ይበልጥ የሚያውቁት በመሆናቸው በተዋረድ ከተኮለኮሉ ብሄርተኞች እና መንደርተኞች መዋቅራቸውን እያጸዱ ካልተጓዙ መንገጫገጩ ይቀጥላል። በመንገጫገጩም ውስጥ ቢሆን በጣም በደማቁ የሚታይ ለውጥ ግን አለ።

  
መጋቢት 30/2011 ብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ የቀረበ




Tuesday, August 6, 2013

የጭለማ ቤት ጓደኞቼ



             የጭለማ ቤት ጓደኞቼ
                                                                    
                                           ሲሳይ አጌና
       ልክ  የዛሬ አምስት ዓመት በጥቅምት 1999 ዓ.ም ዓለም በቃኝ ጭለማ ቤት  የነበሩት  የጭለማ ቤት  ጓደኞቼ ዛሬ ተመልሰው ጨለማ ቤት ከወደቁ አንድ ወር አስቆጠሩ፤ለመብት እና ለነጻነት መቆም፣ለእውነት እና ለፍትህ መሰለፍ፣እኩልነት እና ዲሞክራሲ መጠየቅ በወንጀል ተመንዝሮ፣በአሸባሪነት ተፈርጆ ወህኒ ወርደዋል፤ክሱ የፈጠራ፣ሁሉ ነገር የጨበጣ እንደሆነ ከመነሻው ግልጽ የሆነው የሕወሐት መሪዎች ውሸታሞች መሆናቸው ስለሚታወቅ ብቻ አልነበረም፤ባለፉት ሃያ ዓመታት የፈጠራ ክስ በማቀነባበር፣አሳፋሪ "ማስረጃ" በመፈብረክ ስለሚታወቁም ብቻ  አይደለም፤ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ለመወንጀል እና ሕዝብንም  ለማሸበር  ራሳቸው ፈንጂ እያጠመዱ  በሀገሪቱ የሽብር ድርጊት መፈጸማቸውን በኢትዮጵያ  የአሜሪካ አምባሳደር (ጉዳይ ፈጻሚ)  የነበሩት ቪኪ ሀድልስተን ስላረጋገጡ እንዲሁም የሕወሀት የሽብር ታሪክ በግሎባል ቴረሪዝም ዳታ ቤዝ ላይ ጭምር ስለተመዘገበ ነው።(ቪኪሀድልስተን እ/ኤ/አ አርብ ኦክቶበር 6/2006 ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የላኩትንና ሀሙስ ሴፕቴምበር 1/2011 ዊክሊክስ ይፋ ያደረገውን  መሉ መልዕክት በዚሕ ጽሁፍ መጨረሻ ገጽ ላይ ሰፍሯል፤ከምንጩ ለማየት ከፈለጉ ደግሞ  በዚህ ሊንክ ያገኙታል http://www.cablegatesearch.net/cable.php?id=06ADDISABABA2708&q=ethiopia የሕወሐትን የቀደመ   የሽብር ታሪክ  ደግሞ  በዚህ ሊንክ  ያገኙታልhttp://www.start.umd.edu/gtd/search/Results.aspx?search=Tigray+peoples+liberation+front+%28TPLF%29&sa.x=49&sa.y=20
      የሕወሐት ደህንነቶች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ወንጅለው ለማሰር ሲሉ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ንጹሃንን ፈንጂ አጥምደው መግደላቸው ነው በዊክሊክስ ሰነድ የተጋለጠው፤ምርጫ 1997 በተመሳሳይ ተቃዋሚዎችን ለመወንጀል  ፖሊሶችን  ጭምር  በቦምብ እና በጥይት መግደላቸውን የአጣሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል አጋልጠዋል፤በሃይል እና በጠለፋ  የሪፖርቱን መደምደሚያ ከልሰው ለፓርላማ ባቀረቡት በእነ ዶ/ር መኮንን ዲሳሳ  ሪፖርትም ላይ ሰልፈኞቹ የጦር መሳርያ አለመያዛቸው ተሰምሮበት በፓርላማው ጸድቋል፤ፖሊሶቹ ደግሞ የተገደሉት በጦር መሳርያ  መሆኑ በዚያው ሪፖርት ላይ ተረጋግጧል።"ተራራውን ያንቀጠቀጠው"  እንዲሁም ባለፉት 20 ዓመታት ሕዝቡን በርሀብ እና በሽብር የቀጠቀጠው ሕወሐት ማለት ይህ ነው።
       አንሰበርም ብለው ለሕዝብ መብት እና ነጻነት የቆሙ ወገኖችን ለመወንጀል ሆቴል እና ታክሲ ላይ ፈንጂ እያጠመዱ ንጹሃንን የሚፈጁ  ጨካኞች እያንዳንዱን ሰው ለማሰር አንድ ታክሲ ሙሉ ንጹሃንን ከሚያቃጥሉ የጸረ ሽብር ሕጉ እንኳን ስራ ላይ ዋለ የምለው ከውስጥ በመነጨ ስሜት ነው፤ይሕ ሕግ ባይኖር ኖሮ አቶ በቀለ ገለታን እና ወጣቱን ፖለቲከኛ ኦልባና ሌሊሳን አሸባሪ ብሎ ለማሰር ቢያንስ አንድ ታክሲ በፈንጂ ማጋየታቸው የሚጠበቅ ነበር፤ጋሽ ደቤን (አንጋፋውን አርቲስት ደበበ እሸቱን) ለማሰር አንድ ሆቴል ወይንም ሌላ ታክሲ፣እስክንድር እና አንዱዓለምን ለመክሰስ እንዲሁ ተጨማሪ አውሬያዊ ድርጊት ሊፈጽሙ ይችሉ እንደነበር ከጀርባ ታሪካቸው በመነሳት መደምደም ይቻላል። ...ወደ ጨለማ ቤት ጓደኞቼ ልመለስ...
        ከአምስት ዓመት በፊት ሀምሌ 20 ቀን 1998 ዓ.ም  አንዱ ዓለም አራጌና እስክንድር ነጋ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ነበሩ፤በዚህ ዕለት ከሰዓት ከቀኑ አስር ሰኣት ገደማ እስክንድር ዞን 5 ከሚባለው ስፍራ ተወሰደ፤አንዱዓለምም ዞን አንድ ከተባለው የእስር ግቢ እቃህን ጠቅልለህ ውጣ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ደረሰው፤እስክንድር እና አንዱ ዓለም በፖሊስ መኪና ተጭነው ወደ ቀድሞው ከርቸሌ እስር ቤት  ከተወሰዱ በሗላ ዓለም በቃኝ ጨለማ ቤት ተቆለፈባቸው፤አስቀድሞ  ወደ ጨለማ ቤት ተወስዶ የነበረው ሙሉነህ ኢዩኤልም እንደገና ወደ ጨለማው ተመለሰ፤ትንሽ ሲቆዩ እኔም ደበርኩዋቸውና ነሀሴ 12 ቀን 1998 ከቃሊቲ ወስደው የጨለማው ቤት ማህበርተኛ አደረጉኝ፤ጓደኞቼ በሞቀ ወሬ ተቀበሉኝ፤እያወራን እኩለ ሌሊትን ተሻገርን፣ሊነጋ ሲል በእንቅልፍ ተሸነፍኩኝ፤ከእንቅልፌ ነቅቼ  ዙሪያውን ሳማትር ግድግዳው በጽሁፍ ተሞልቷል፤"ከዚህ ሕይወት አንድ ገመድ አይሻልም ወይ ?" የሚለው ሳይደበዝዝ በደማቁ ይታያል፤በብቸኝነት የስቃይ ሕይወት ተማሮ  ገመድ የተመኘውና ገመድም አጥቶ ምኞቱን እዚያ ጭለማ ቤት ትቶ ተራውን ለኛ የለቀቀው ማን እንደሆነ አላወቅንም፤ዘግይቶ በደረሰን መረጃ እዚያ ክፍል ውስጥ የነበሩት ሻለቃ ጸሃዬ  ወልደስላሴ ነበሩ፤ሻለቃ ጸሀዬ ወልደስላሴ ሕወሐትን በአፍላው ዘመን በ1968 ተቀላቀሉ፣እስከ ግንቦት 4 ቀን 1994 ከሕወሀት ጋር ቀጠሉ። (መከላካያ ሰራዊቱ ከፖለቲካ ነጻ የሚሆነው ወረቀት ላይ ብቻ መሆኑ ይታወቃል)
            ሻለቃ ጸሃዬ በየካቲት ወር 1993 ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሐት) ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች  ስብሰባ ላይ የስብሰባውን መሪና  የደህነነት ሚኒስትሩን አቶ ከንፈ ገ/መድህን በጥይት ገድለዋል በሚል ታሰሩ ፤ ሻለቃ ጸሀዬ  በቅድሚያ በማዕከላዊ ምርመራ ፣በሗላም በዓለም በቃኝ ፣በመጨረሻም በቃሊቲ  ከ 6 ዓመታት በላይ ጨለማ ቤት አሳልፈዋል፤እኚህ ሰው ከግንቦት 4 ቀን 1993  እስከተገደሉበት ቀን ድረስ  6 ዓመት ከ2 ወር ከ26 ቀን የታሰሩት ለብቻቸው ነበር፤...ሃምሌ 29 ቀን 1999  ሌሊት የቃሊቲ እስር ቤት ሃላፊዎች  ሻለቃ ጸሀዬ መኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ "ሻለቃ ጸሐዬ ስለታመመ መጥተሽ እዪው " በማለት   ባለቤታቸውን ይዘዋቸው ይሄዳሉ፤ሴትየዋ ዛሬ ወደማያስታውሱት አንድ ግቢ አስገብተው ወደ አንድ ክፍል እያመላከቱ "እዚያ ክፍል ተኝቷል፤ግቢና አነጋግሪው" ብለው ይመርዋቸዋል፤ባለቤታቸውን ሻለቃ ጸሀዬን  ሊያነጋግሩ የገቡት  ወይዘሮ  የጠበቃቸው በደም የጨቀየ የባለቤታቸው አስክሬን ነበር፤ሕወሐት እንዲህም ነው።
         ስለጨለማ ቤት ጉዋደኞቼ ሳነሳ የጨለማ ቤቱ ግድግዳ ፊቴ ላይ ተደቅኖ ብዙ ርቀት ወሰደኝ፤በዘረኝነት እያበዱ ከነቁሻሻው ሕወሐትን የሚደግፉ፣ሺህ ዘመን እሱ ይግዛን በማለት ለአቶ መለስ ውዳሴ የሚያቀርቡ (በቨርጂኒያ አርሊንግተን  የነበረውን ውዳሴ እና ጭፈራ ልብ ይሏል፤ በዚህ ሊንክ  ያገኙታል፤     http://www.youtube.com/watch?v=XW5jvUV2T04) ሕወሀት እና አቶ መለስ ከዘረኝነታቸው ባሻገር ጭካኔያቸው በርሃ ወርደው በመከራ ውስጥ ባለፉት ላይ ጭምር መሆኑ የሚከሰትላቸው መቼ ይሆን? ወይንስ ሻለቃ ጸሀዬ ዘራቸው ሲቆጠር  ሌላ ሆኖ ተገኘ? በሻለቃ ጸሃዬ  የተገደሉት  የአቶ ክንፈ ገብረመድህን ደም ደመ ከልብ ይሁን እያልኩ አይደለም፤አቶ ክንፈን የገደለ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከገደለ ወንጀለኛ በተለየ ለምን ሰቆቃ ይፈጸምበታል? ነው ጥያቄው።ገዳይም፣ሟችም የታገሉለት  ሥርዓት በኢትዮጵያ ምድር ጥላቻ እና ሰቆቃ ያነገሰ፣ዕኩልነትን የገሰሰ መሆኑ ጸሃይ በወጉ ያገኘው ዕውነታ ቢሆንም፣ሰብኣዊና ሕጋዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት አምናለሁ።
       በኢህአዴግ የ20 ዓመታት አገዛዝ  የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው አስረኞች በተረጋገጠ መረጃ ሁለት ብቻ ሲሆኑ፣እነርሱም ጄኔራል ሃየሎም አርአያን የገደለው ጀሚል ያሲን እና አቶ ክንፈን የገደሉት ሻለቃ ጸሀዬ ወልደስላሴ ናቸው፤ሌሎች ሁለት እና ሶስት ሰው ገድለው ሞት የተፈረደባቸው በርካታ ሰዎች በወህኒ ቤት ውሰጥ ሲኖሩ፣አንዳንዶቹ ሞት ፍርዱ ከጸናባቸው 17 ዓመታት አልፏቸዋል፤ሁሉም ሰዎች እኩል ቢሆኑም ሕወሐቶች የበለጠ እኩል ናቸው እና የሆነው ሁሉ መሆን የሚገባው ነበር።በነገራችን ላይ በሌሎቹ ላይ ለምን ሞቱ ተፈጻሚ አልሆነም እያልኩ ሳይሆን፣የሕወሐት መዝገበ ቃላት ሰው የሚለውን ቃል ሕወሐት በሚል የሚፈታው  መሆኑን ለማሳየት ብቻ ነው፤እርግጥ ነው ሻለቃ ጸሃዬ ለ6 ዓመታት ከሰው ሳይገናኙ የውስጣቸውን በውስጣቸው እንደያዙ መገደላቸው ከግድያው ጀርባ ማን አለ?የሚለውን ጥያቄ በብርቱ ያስነሳል፤አቶ ክንፈ የተገደሉበትን ስብሰባ ሊመሩ ከመነሻው ፕሮግራም የተያዘላቸው አቶ መለስ ዜናዊ  አቶ ክንፈን ልከው ርሳቸው መቅረታቸው የአጋጣሚ ተብሎ እንዳይታለፍ ሻለቃ ጸሃዬ ከሰው ሳይገናኙ  6 ኣመታት በጨለማ ማሳለፋቸው እንዲሁም የሚሊኒየሙ ይቅርታ በታወጀበት፣የቅንጅት መሪዎች በተፈቱ በ17 ኛው ቀን መገደላቸው አብዝተን እንድንጠረጥር ጠልቀን እንድንመረምር የሚያደርግ ነው፤ለህወሀት ቅርብ የሆኑ ሰዎች ሴራ አለ የሚለውን ቢያጣጥሉም።....
        አልፎ አልፎ የምጽፋቸውን ጽሁፎች የተመለከተ አንድ ታዛቢ የተለያዩ ርዕሶችን አንድ ላይ አትደርት ለየብቻቸው ጻፋቸው ያለኝ ትዝ ስላለኝ ርዕሴ  ሕወሀት እና ሻለቃ ጸሀዬ  ከመሆኑ በፊት ልመለስ፤ ...አዎን ሻለቃ ጸሃዬ የነበሩበትን ጨለማ ቤት ዛሬ ተመልሰው ጨለማ ከተጣሉት እስክንድር እና አንዱዓለም እንዲሁም ዛሬ በውጭ ከሚኖረው ሙሉነህ ኢዩኤል ጋር በ1998 ክረምት  ተረከብን፤ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ በ17 የማጭበርበር ወንጀል  ተከሶ  ከወህኒ ቤት ያመለጠ ወርቁ የተባለ ሰው ሲያዝ ጨለማውን ለሱ ለቀን ለእኛ ቆርቆሮ ቤት ተቀለሰልን፤አንድ የኮንፈረንስ ጠረጴዛ የምታህል ግቢም ታጠረልን፤ዓለም በቃኝ ወህኒ ቤት  ያረፈበት ስፍራ ለአፍሪካ ሕብረት አስቀድሞ በመሰጠቱ ሕብረቱ  ግንባታውን ሲጀምር  በህዳር ወር 1999 ከጠባቡ ወህኒ ቤት ወደቃሊቲ ተጭነን ከሌሎች አባሪዎቻችን ጋር ተቀላቀልን፤ከወራት በሗላ ሁላችንም ወደ ሰፊው እስር ቤት ተለቀቅን፤በተፈታን በአምስተኛው ዓመት እስክንድር እና አንዱአለም አሸባሪ የሚል ስም ወጥቶላቸው እንደገና ወደ ጨለማ ቤት ተመለሱ፤ከነርሱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ታዋቂው የቲያትር ባለሙያ እና ፖለቲከኛ  አርቲስት ደበበ እሸቱ  በ70 ዓመቱ በአሸባሪነት ታሰረ።
         ጋሽ ደበበ  እንዲሁም በህዳር 1999  በአፍሪካ ሕብረት ሳቢያ ከጠባቡዋ እስር ቤት የወጡት አንዱዓለም እና እስክንድር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ሚኖርበት የቁም እስር የተሸጋገሩት  ወይንም ከቃሊቲ የወጡት ሽምግልና  እና ይቅርታ የሚል ኮተት ቢንጠለጠልለትም እውነታው እና በዊክሊክስ ሰነድ በዲፕሎማሲያዊ ቃና  እንደተረጋገጠውም በአሜሪካ መንግስት ግፊት ነበር፤እንዲያውም እስክንድር ከሁለት ወራት ቀደም ብሎ በነጻ የተለቀቀ ቢሆንም፣የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተያዘ እለት ምሽት በይቅርታ ነው የወጣው በማለት ዘግበዋል፤ሁሉ ነገረ በደመነፍስ ስለሆነ  የእስክንድር እና አንዱዓለምን እንዲሁም የጋሽ ደበበን፣የአቶ በቀለ ገለታን፣የአቶ ኦልባና ሌሊሳን፣የነክንፈሚካል ደበበን  ወዘተ አሸባሪነት የሚያስረዳ  በቶን የሚቆጠር መረጃ እንዳላቸው ሰሞኑን አቶ መለስ  የዓመቱን ዕቅድ ለፓርላማ ሲያቀርቡ እንሰማለን፤ለመዋዕላ ሕጻናት የማይመጥን የመከነው ሽብር  ወይንም ሌላ ስም የሚሰጡት ቲያትር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እናያለን።...አርቲስት ደበበ እሸቱ፣.አንዱዓለም እና እስክንድር ከግንቦት 7 የተቀበሉት መመሪያ እና ለአሜሪካ ወይንም ለእንግሊዝ መንግስት፣ምናልባትም ለኤርትራ የስለላ ተግባር ሲያከናውኑ እንደነበር የሚያስረዳ በጌታቸው አሰፋ ወይንም በኢሳይያስ ወልደጊዮርጊስ የተደረሰ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሚተረክ ፎርጀሪ እና ቀሽም ዶክመንተሪ በነጻ ያሳዩናል፤ለተመልካቹ ሳይከፍሉ ለማለት ነው።
      የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን አዘውትሮ ማየት አይኪው ዝቅ ያደርጋል ይል ነበር እስክንድር።በርግጥም ሆድ በርሃብ እየጮኸ፣ሕሊና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተራቆተ ደስታ እንደራቀን ስቃዩ የሚቀጥለው እስከመቼ ይሆን? በርግጥ ደልቷቸው የሚስቁ፣ባርነት ተመችቷቸው  የሚገለፍጡም አልታጡም፤መቼም በባርነት ስር ሆኖ የሚደሰት አዕምሮው ማፍሰስ የጀመረ እንጂ ሙሉ ጤነኛ ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፤ሳቅ ሲነሳ ከዓመት በፊት የነበረው የእስክንድር የሳቅ ምኞት ታወሰኝ፤ ቦሌ መንገድ ዓለም ሕንጻ  ከሚገኘው ላፓሬዚያን ካፌ  በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን  ማኪያቶ እንጠጣለን፤ያው እንደ ሁሌው  ፖለቲካውን ስንሰልቅ ከአጠገባችን ያሉት ጎረምሶች በሳቅ ያውካካሉ፤አንዳንዶቹ ከምር በሳቅ እየፈረሱ ነበር፤ጨዋታቸው የደራ ነውና ትኩረታችንን ስበዋል፤. "እኛ መቼ ነው የምንስቀው ?" በሚል  እስክንድር  ለወረወረው ሃሳብ  በወቅቱ ምላሽ አልነበረኝም፤ ግን አንዳንዴ ሳስበው የሚታኘክ በሌለበት፣ደስታ በጠፋበት ጥርስ ራሱ በኢትዮጵያ ምን ያደርጋል? ...
         ሳቅ እየናፈቀው  ጨለማ ቤት የሚንከራተተው እስክንድር ነጋ የወርቅ ማንኪያ ጎርሰው  ከተወለዱ  የሃብታም ልጆች አንዱ ነው፤የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የጀመረው ዛሬ የአቶ መለስ ልጆች በሚማሩበት እንግሊዝ ስኩል ሲሆን፣የሁለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ ትምህርቱን የተከታተለው በዩ.ኤስ አሜሪካ ነበር፤በዚህ ሂደት ያለፉ ሰዎች (ያ ትውልድን አይጨምርም) በአብዛኛው ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ግኑኝነት የላላ እንደሆነ በስፋት ሲታመን፣እንደ ኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ መግባት በእነሱ ዓይን የጤንነት ምልክት ተደርጎ የሚታይ አይደለም፤የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲፈነዳ የቦሌ ልጆች  "እኛ ምን አገባን  የጨርቆስ ፣የፈረንሳይ እና የሽሮሜዳ ልጆች ይቸገሩበት " አሉ ተብሎ እንደተቀለደው ወደ እስር ቤት መወርወር እና መከራ መቀበል እንደኛ  የኔታጋ ፊደል ቆጥረው አምሃ ደስታ እና መሰል የመንግስት ት/ቤት ለተማሩ እንጂ በርግጥም በእንግሊዝ ስኩል ላለፉ ከባድ ቢሆንም፣እስክንድር በአቶ መለስ የ20 ዓመታት አገዛዝ ለ8ኛ ግዜ እስር ቤት ገብቷል፤ጨለማ ቤትም ተጥሏል።
        በጥቅምት 1985 የፕሬስ ነጻነት መታወጁን ተከትሎ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ኢትዮጲስ ጋዜጣን በማቋቋም  ከሟቹ ታዋቂ ጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ጋር በነጻ ፕሬስ ውስጥ የሚታይ ደማቅ አሻራ አሳርፏል፤በመቀጠል ሀበሻ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ፣በሗላም ምኒሊክን ጨምሮ ሶስት ጋዜጦችን በማቋቋም  እስከ ጥቅምት 1998 ሲሰራ  ቆይቷል፤ምርጫ  97ትን ተከትሎ በህዳር 1998 ለ 7ኛ ግዜ ወደ እስር ቤት ተወሰደ፤አሁን ለ8ኛ ግዜ። በዚህ ሂደት በተለይም በ1988ቱ  እስራት ወቅት ባዶ ክፍል ቀዝቃዛ ወለል ላይ እንዲተኛ በማድረግ እንዲሁም በተፈጸመበት ድብደባ በእጁ ላይ  ውልቃት ደርሶበታል፤አሁንም የችግሩ ሰለባ እንደሆነ ቀጥሏል።በ1998 እስክንድርን ለማሰር ስሙ በጋዜጣ አዘጋጅነት ስላልሰፈረ እንዲሁም በባለቤትነትም እንዳይጠይቁት ምንም ቀዳዳ ሲያጡ ጨርሶ አባል ባልሆነበት የቅንጅት አመራር በማለት ከሰሱት፤አንድ ዓመት ከ6 ወር ታስሮ በነጻ ተለቀቀ፤በጋዜጣ ስራም እንዳይሰማራ በፖለቲካ ውሳኔ ታገደ።
     የሕወሐት መሪዎች ያኔም ዛሬም እስክንድር ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግኑኝነት እንደሌለው  ያውቃሉ፤አሁን በግንቦት 7 ፈርጀውት በአሸባሪነት ሲከሱትም ከግንቦት 7 ጋር ግኑኝነት አለው ብለው በማመን ሳይሆን፣በኢንተርኔት እና በሀገር ቤት አንዳንድ ጋዜጦች ላይ የሚጽፈው ዕውነት ስላንገሸገሻቸው፣ትንተናው ስላባነናቸው ብቻ ነው፤.የአሁኑ እስራት የቅንጅት መሪዎች በተፈቱበት ወቅት አቶ መለስ ለሕወሐት ሰዎች ተናገሩ የተባለውን ያስታውሰናል፤በምዕራባውያኑ የተደረገውን ግፊት ተከትሎ የቅንጅት መሪዎችን ለመፍታት እና በፖለቲካው ሂደት እንዲቀጥሉ የሕወሀት አመራር ሲወስን፣የፖለቲካው አካሄድ የማይገባቸው የሕወሀት ጄኔራሎችና ሌሎች ሕወሐቶች አኩርፈው ነበር አሉ፤ አቶ መለስ ለነርሱ የሰጡት ማጽናኛ "አታስቡ እግር እስኪያወጡ እንጠብቃቸዋለን፤ሊራመዱ ሲሉ እግራቸውን እንቆርጠዋለን" የሚል ነበር ፤ከሕወሀት ውጭ ያለውን አንድም በአሽከርነት አሊያም አዋርደው ለመግዛት የተነሱት የህወሀት መሪዎች  ሁሉንም ለመስበር ቀና ያለውን መቀንጠስ ያስፈልጋል በሚል የወሰዱት  ርምጃ ነው።
            የማርቲን ሉተር ኪንግ አድናቂ፣ሰላማዊ ትግል ላይ የቆረበውንና ባለፉት 12 ዓመታት በዚሁ የትግል መስመር ላይ ጸንቶ የቆመውን አንዱዓለም አራጌን በአሸባሪነት መክሰስ፣ከሳሾቹ ደግሞ  በዓለማቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት የተመዘገበው የሕወሀት  መሪዎች መሆናቸው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ነው፤አስገራሚው ነገር መንግስት ሆነውም በዚሁ የሽብር ድርጊታቸው መቀጠላቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ ሰነዶች ባረጋገጡበት እነ አንዱኣለምን በሽብር መክሰስ የሕወሐት የደመነፍስ ጉዞ አሁንም እየተወለካከፈ መቀጠሉን ከማሳየት ውጭ የሚጨምረው ነገር የለም፤ዛሬ የህወሀትን ውንጀላ የሚያምኑ በዘር ጥብቆ ውስጥ ገብተው ጉድጓድ ውስጥ እንዳለችው እንቁራሪት ሰማዩ የጠበበባቸው የሕወሀት ሰዎች  ብቻ ናቸው።
           አንዱዓለም በ1990 ዎቹ መጀመሪያ በአዲስ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ካውንስል አመራር ነበ ር፣የፖለቲካ ተሳትፎውንም ከ1992 ጀምሮ በፓርቲ በመታቀፍ ቀጥሏል፤በኢዴፓ ምክትል ጸሐፊነት፣በቅንጅት ለዕላይ ምክር ቤት አባልነት አገልግሏል፤በምርጫ 2002 የፓርቲዎች ክርክር  የምርጫውን ሙቀት በመጨመር ብዘዎች ያስታውሱታል፤በዚያ የፓርቲዎች ክርክር የተናገረው የተቆረጠበት ብቸኛ ተከራካሪም እርሱ ነበር፤አሁን የኢህአዴግ አጋር ፓርቲ አመራር በመሆን በተገቢው ቦታ ላይ የሚገኘው የኢዴፓው ልደቱ አያሌውን በተመለከተ የተናገረው እንዲሁም ሬድዋን  ሁሴን የተባለ ኢህአዴግን በወዶገብነት የተቀላቀለ ግለሰብ ከተቃዋሚነት ወደ ኢህአዴግ ያደረገውን ሽግግር የተቸበት ክፍል ተቆርጦ ወጥቷል፤ቃሊቲ እስር ቤትን ከደቡብ አፍሪካው ሮቢን አይላንድ ጋር በማነጻጸር የቃሊቲን ሲኦልነት የገለጸበትም እንዳይተላለፍ ታግዷል፤ምርጫ 1997ትን ተከትሎ በተወሰደው የእስራት ርምጃ አንዱኣለም እስር ቤት ቤት  ብቻ ሳይሆን ጨለማ ቤት ተጥሏል፤ከጨለማ በተጨማሪ አደገኛ ቦዘኔ ዞን በተባለው የእስር ሰፍራ ተወስዶ የታስረ ብቸኛ የቅንጅት እስረኛ ነበር፤የቅንጅት መሪዎች የፈረሙበትን የይቅርታ ወረቀት አንፈርምም ብለው ካንገራገሩትም አንዱ አንዱዓለም ነው፤...ለፈው እንግልት አልበቃ ብሎ ከሁለት ሕጻናት ልጆቹ ሩሕ እና እጹብ ነጥለው መልሰው ጨለማ  ውስጥ  ጥለውታል፤እስክንድርንም እስር ቤት ከተወለደው የ 5 ዓመት  ሕጻን ልጁ  ናፍቆት ነጥለው ነበር  በሰንሰለት አስረው የወሰዱት።    
         ሽብር ሲነሳ ዓለም አልቃይዳን እና ቢንላደንን በዋናነት ያስታውሳል፤ሕወሐት ደግሞ  ኦነግ እና ኦብነግን ይጠቅሳል፤አሁን ደግሞ ግንቦት 7 ተጨምሮበታል፤እድሜ ለዊክሊክስ እና  ለግሎባል  ቴረሪዝም ዳታቤዝ በሽፍትነቱም፣በመንግስትነቱም አሸባሪው ሕወሐት መሆኑን አጋልጠዋል፤   የዊክሊክስ ምስጢራዊ ሰነዶች የህወሐትን መንግስታዊ አሸባሪነት ከማጋለጥ ባሻገር ብዙዎች በአሜሪካ መንግስት ላይ የነበራቸውን  ቅሬታም የገፈፈ ሆኖ አልፏል፤አዲስአበባ ላይ የተፈራረቁት የአሜሪካ አምባሳደሮች ህወሃት ደጋፊ የሆኑት ቪኪ ሀድልስተንን ጨምሮ  ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የጠራ እና የተብራራ ሪፖርት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን  እድሜ ለዊክሊክስ ተረድተናል፤የአንድ ዘር አገዛዝ በሀገሪቱ መስፈኑን፣የሌሎች ሚና የአጫዋችነት መሆኑን በዝርዝር ደጋግመው ጽፈዋል፤ የሕወሐት መሪዎች ሰዎችን በሀሰት ወንጅለው እንደሚያስሩሌላው ቀርቶ ሰዎችን ለማሰር ሲሉ ፍንዳታ እንደሚያቀነባብሩ  እድሜ ለዊክሊክስ ሁሉም ተገለጠ።
          እዚህ ላይ ሌላው በደማቁ የሚሰመርበት ነጥብ በሕወሃት ሰዎችና አደግዳጊዎቻቸው  አቶ መለስ  ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ አላቸው በሚል ሲለቀቅ የነበረው ነጠላ ዜማ  ወደ ተረተትነት መቀየሩ ነው፤ዲፕሎማቶቹ በአቶ መለስ ንግግር ያመኑ መስለው በአደባባይ እየለፈፉ፣እየተየቡ የሚልኩት  ሌላ መሆኑ  በቂ ብርሃን አግኝቷል፤የአቶ መለስ የንግግር ችሎታ የማይካድ ቢሆንም፣ ብዙ ግዜ የማሳመኛ  ነጥባቸው  ወይንም መከራከሪያቸው የይሉኝታ ገደብን ያለፈ፣በስድብ የታጀበ እንደሆነም  በግልጽ ይታወቃል፤በጄኔቭ የአሜሪካ አምባሳደር ዳግላስ ግሪፍዝስ በኢትዮጵያ የአንድ ዘር የበላይነት ስለመግነኑ በማንሳት፣ይህም ችግር ያስከትላል በማለት በሰብዓዊ መበት ኮሚሽን ጉባኤ ላይ የዛሬ 3 ዓመት ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፤ይህንን በተመለከተ በታህሳስ 2001 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተጠየቁት አቶ መለስ ዜናዊ ዕውነታውን ከመካድ ባሻገር አሜሪካዊውን ዲፕሎማት ደደብ ማለታቸው በአደባባይ የተነገረ ነውና ብዙዎች ያስታውሱታል፤ ገሃዱን ዕውነታ በስድብ ለማስተባበል መፍጨርጨር፣ይህ ግፍና ውርደት ከዚህ በላይ ለማስቀጠል መታበይ አጸፋው የውርደት ውርደት እንደሚሆን ቀኑን አንወቀው እንጂ ሳይታለም የተፈታ ነው፤መውደቃችሁን የሚጠራጠር እርሱ ሕሊናው የዘረኝነት ሞራ የለበሰ፣እንዲሁም በጥቅም አብዶ አዕምሮው ያፈሰሰ ብቻ ነው፤ሌላው እንዳትወድቁበት ይጠነቀቃል እንጂ ሩቅ በማይባል ግዜ መውደቃችሁን አይጠራጠርም።የአፍሪካ ንጉሰ ነገስትነትን ሲያልሙ ሲርቲ ጉድጓድ የወደቁትን ጋዳፊን ያየ በስልጣን  ይጫወታልን?ለመሆኑ የአቶ መለስ ሲርቲ  የት ይሆን? አድዋ ወይንስ ቻይና?
                       እነሆ አድራሻዬ፦  lualawi2000@yahoo.com
                                                                                                                                                                                        ጥቅምት 6/2004